ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ልምድ መውሰዷ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸውን ቆይታ በተመለከተ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት በኮሪያ ሪፐብሊክ እየተደረገ ያለው ጉብኝት ኢኮኖሚን የሚያጠናክር ነው። በተለይ ባለፋት 70 ዓመታት ደቡብ ኮሪያ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቅ ልምድ የሚወሰድባት ሀገር ናት።

በሀገሪቱ ያለውን ልምድ ከመቅሰም ባሻገር የኮሪያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ስለመደረጉ አስረድተዋል። በተለይም ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እያለሙ የሚገኙ ባለሃብቶችን በመጠቀም ተጨማሪ ባለሃብቶች እንዲገቡ ለማድረግ ስኬታማ ሥራ ስለመሠራቱ አስገንዝበዋል።

በተለይም በኮሪያ ያሉ የሥራ ኀላፊዎችን በማግኘት በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ ሁኔታ ገለጻ ስለመደረጉ ነው ያስገነዘቡት። ቀደም ሲል ውጤታማ የኾኑበት የቴክስታይል እና ጋርመንት ሥራ በሌሎች አማራጮች እየተያዙ በመምጣታቸው ወደ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ እና ቻይና እየሄዱ መኾኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ አለበል ወደ ኢትዮጵያም የመምጣት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ ጥሬ እቃ የምታስገባው ከተለያዩ ሀገራት በመኾኑ በተለይም ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ምቹ በመኾኗ በስፋት ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ ስለመደረሱ ነው ያብራሩት። ከሀገሪቱ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ያለውን ግንኙነት በማጠናከር አብሮ እንደሚሠራም መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በቡና ዘርፍም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከምንጩ እሴት ጨምረው ቡናን የማቀነባበር ሥራ እንዲሠሩ መግባባት ላይ ስለመደረሱም ነው የገለጹት። የብረት ፋብሪካን በተመለከተም ልምድ ያላቸው በመኾኑ እና ኢትዮጵያም የብረት ሀብቷ ያልተነካ በመኾኑ ልምዳቸውን ተጠቅመው እንዲያለሙ ጥሪ የቀረበላቸው ሲኾን እነሱም ጥሪውን ተቀብለው በመምጣት ለማልማት እና ጥናት ለማድረግ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መስማማት ላይ ስለመደረሱ ተናግረዋል።

ስማርት ሲቲን በተመለከተም እንደ ሀገር የተጀመረውን ሥራ ከኮሪያ ተወሰዶ ለማስፋት እና አብሮ ለመሥራት ስለመነጋገራቸውም ነው ያስገነዘቡት። የሎጀስቲክስ እና የወደብ አገልግሎታቸው እጅግ የዘመነ በመኾኑ ከዚህም ተሞክሮ ስለመወሰዱ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ እጅግ ፈጣን ኢኮኖሚ እና ልማት ያላቸው ሀገራት ከኮሪያ ልምድ መውሰዱ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ነው ያብራሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ልዑካቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ ያደረጉት ጉብኝት ትክክለኛ እና ልምድ ሊወሰድባቸው ከሚገቡ ሀገራት አንደኛዋ እንደኾነች መመልከታቸውንም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የደብረ ብርሃን መኪና መገጣጠሚያን መረቁ።
Next articleየሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የቢዝነስ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ ነው።