
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ማርን በብዛት እና በጥራት ለማምረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ገልጿል። በአማራ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የንብ መንጋ እንዳለ እና ይህም የሀገሪቱን 20 በመቶ እንደሚሸፍን በ2015 ዓ.ም የተደረገ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ጥናት ያመላክታል። በክልሉ 482 ሺህ አናቢዎችም አሉ።
አርሶ አደር ካሣየ ምድራለም በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ጋፍቲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተዋል። ሙያውን ከአባታቸው እንደተማሩት የተናገሩት አርሶ አደር ካሳየ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የሙሉ ጊዜ ሥራ እና መተዳደሪያ አድርገውታል። ”የበልግ ዝናብ ከጣለ ግንቦት ወር ማር የሚመረትበት ጊዜ ነው” ያሉት አቶ ካሣዬ ለመጪው ጥቅምት ወርም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። ክረምት ለንብ ምቹ ስላልኾነ እንክብካቤ አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
ከባሕላዊ ቀፎ እስከ ሦስት ኪሎ ግራም ብቻ የሚገኝ ሲኾን ከዘመናዊ ቀፎ ግን እስከ 28 ኪሎ ግራም ማር እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደር ካሳየ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ነጻ በኾነ መሬታቸው ጭምር እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ የአበባ አትክልቶች እና ቅመማ ቅመሞች ይተከላሉ፣ ንብ ከባሕላዊ ቀፎ ወደ ዘመናዊ ቀፎ ይገለበጣል፣ በቀፎ ውስጥ ለንቦቹ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራም ይሠራል ብለዋል አርሶ አደር ካሣየ። የባለሙያ እገዛ እንደሚደረግ ጠቅሰው አይነ ርግብ እና ጓንት እንዲቀርብም ጠይቀዋል።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ ቃጩር ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር አሕመድ ሁሴንም ማር ማምረትን በሙሉ ጊዜ ይሠራሉ። አብዛኛው ቀፏቸውም ዘመናዊ ነው። አሁን ላይ በአካባቢያቸው ያለው የበልግ ዝናብ ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ በሰኔ ወር በዱር የሚጓዝ ንብን ለመያዝ ቀፎ የሚዘጋጅበት፣ ለንቦች ተደራቢ የሚደረብበት፣ ለባሕላዊውም ቀፎ የእናት ንብ ማገጃ በመጨመር ተጨማሪ ቦታ የሚደረብበት ጊዜ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የንብ ማነቢያ ቁሳቁስ፣ የማር ማሸጊያ እና የሰም መሸጫ ገበያ የማፈላለግ እገዛ እንዲደረግላቸው አናቢዎቹ ጠይቀዋል። በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ እና ሐር ልማት ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን 29 ሺ 331 ቶን ማር መመረቱን እና በ2016/17 የማር ምርት ዘመን ደግሞ 31 ሺህ ቶን ለማምረት መታቀዱን ገልጸዋል።
በ2016/17 የማር ምርት ዘመን አናቢዎች መለየታቸውን ገልጸዋል። 30 ሺህ ዘመናዊ ቀፎ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 14 ሺህ 500 መሰራጨቱን ተናግረዋል። 16 ሺህ 400 ኢትዮ ርብራብ የሽግግር ቀፎ መቅረቡንም አክለዋል። እንደየ አካባቢው ሁኔታ ቢለያይም ወቅቱ ሲደርስ ንብን የመገልበጥ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በ2015/16 የምርት ዘመን 15 ሺህ ወጣቶች ተደራጅተው ቀፎ እና ግብዓቶች የቀረበላቸው ሲኾን በ2016/17 ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በግንቦት ወር ለወረዳ ባለሙያዎች ሥልጠና እና የሥራ አቅጣጫ መሰጠቱን የጠቆሙት ባለሙያው የሽግግር ቀፎ ሳምንት ታውጆ በባለሙያ ክትትል እየተመራ ነው ብለዋል። የሚዛወረውን ያህል ቀፎም እየተዘጋጀ ነው።
የማነቢያ ቁሳቁስ እና የማር ማሸጊያ ፍላጎትን ከግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅትም ኾነ ከሌሎች አቅራቢዎች ላይ ማግኘት እንደሚቻል ባለሙያው ጠቁመዋል። የሰም ምርትም የጥራት ችግር ከሌለበት በስተቀር በአማራ ክልል ተፈላጊ መኾኑን ነው የገለጹት። ከማር ምርቱ ቀድሞ ቅድሚያ ክፍያ ተከፍሎበት እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል።
ሥልጠናውን እስከ አናቢዎች ለማድረስ የበጀት እጥረት እና የቀፎ አቅርቦት ችግር እንዳለ የጠቀሱት ባለሙያው ያሉትን ምቹ እድሎች በመጠቀም የማር ምርትን በብዛት እና በጥራት ለመጨመር ጥረት መደረጉን ግን እንደሚቀጥል አስረድቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
