
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የተፋጠነ አጋርነት ለታዳሽ ኢነርጂ ልማት በአፍሪካ” በሚል መሪ መልእክት የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው። የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ የታዳሽ ኢነርጂ ፍላጎትን በተግባር ለማሳደግ በመስከረም ወር 2023 በናይሮቢ-ኬንያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ መጀመሩን አስታውሰው በተፋጠነ አጋርነት ታዳሽ ኢነርጂ በአፍሪካ ለማራመድ ቁርጠኛ የኾኑ ዓለም አቀፍ ሀገራት እና ባለድርሻ አካላት መተባበራቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውኃ ኃይል፣ የንፋስ ኀይል እና የፀሐይ ኀይል አቅም እንዳላት ገልጸዋል። ምክክሩ ከዓለም አቀፍ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በሀገራችን መዘጋጀቱ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ጠቃሜታው የጎላ ነው ብለዋል። ሚኒስትሩ አያይዘውም የታዳሽ ኢነርጂ ሃብቶችን በመጠቀም የአፍሪካ የኢነርጂ እጥረትን ከመቀነስ ባሻገር ለአየር ንብረት የማይበገር ኢንዱስትሪ ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።
አፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የታዳሽ ኢነርጂ ሃብት ክምችት ለመጠቀም የሚያስችል የተመቻቸ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነቶች ምክንያት የ2063 አጀንዳ ለማስፈጸም ተግዳሮት መኾኑንም አንስተዋል። ሚኒስትሩ የኢነርጂ አጋርነት ለማጠናከር ድጋፍ ያደረጉት የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትሰ፣ የአሜሪካ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመሥግነዋል።
በመጨረሻም ምክክሩ ሁሉን አቀፍ የጋራ የማስፈጸም ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሐ ግብር ለመወሰን የሚያስችል በመኾኑ ተሳታፊዎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መልእክት ማስተላለፋቸውን ከሚኒስቴሩ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
