በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የአንድ ኮር ስታፍ አባላት ለተማሪዎች ዩኒፎርም እና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባዕከር አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ ሠራዊቱ የሀገሩን ደኅንነት በመጠበቅ የልማት ሥራዎችን ከማስቀጠል ተልዕኮው ባሻገር ያለውን በማካፈል፣ የተቸገሩትን በመርዳት እና የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን ሕጻናት በማስተማር ለቁም ነገር እያበቃ መምጣቱን አስረድተዋል።

ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣች በትውልድ ቅብብሎሽ የምትቀጥል ስለኾነ ዛሬ የኮር ስታፍ የሠራዊቱ አባላት በባዕከር አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙ 118 የአቅም እጥረት ላለባቸው ተማሪዎች ዩኒፎርም እና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ የተማሪዎችን ዓላማ እና ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል መኾኑን ብርጋዲር ጀነራል ወርቅነህ ገልጸዋል።

የባዕከር ከተማ አሥተዳዳሪ ክፍሌ ዘውዴ ሠራዊቱ ለሰላም እየከፈለ ያለው መሰዋዕትነት እና በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና አቅመ ደካሞችን እና ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመደገፉ ሕዝባዊ ሠራዊት መኾኑን የሚያረጋገጥ ነው ብለዋል። ለተደረገው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል። ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል እመቤት ወርቅነህ እና ወረቀት አድማሱ መከላከያ ሠራዊት ማለት እኛን የሚጠብቅ እየሞተ ሰላምን እና ልማትን የሚያስቀጥል የሕዝብ ልጅ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ድጋፉ ምቹ የመማር ማስተማር ምቹ ሂደት እንዲኖር የሚያስችል በመኾኑ ለተደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተሰናዱ እመቤት፤ የተዋቡ ንግሥት”
Next articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ !