“የተሰናዱ እመቤት፤ የተዋቡ ንግሥት”

60

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከውበት የላቀ ውበት ተሰጣቸው፣ ከደም ግባትም የተወደደው ታደላቸው፣ ከብልሃትም የላቀውን ብልሃት ተቸራቸው። እረኞች ያዜሙላቸዋል፣ የዓለም አጫዎቾች ይቀኙላቸዋል፣ መኳንንቱ እጅ ይነሱላቸዋል፣ መሳፍንቱ ለክብራቸው ያረበርቡላቸዋል። ወይዛዝርቱ ሽቶ ይዘው ያርከፈክፏቸዋል። ጎበዛዝቱ በክብር ይጠሯቸዋል። የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የቤተ መንግሥት ጠባቆች በጀግንነት ያጅቧቸዋል፣ ይጠብቋቸዋል።

ንጉሥ በደም ግባታቸው ተማርከዋል፣ በፍቅራቸው ወድቀውላቸዋል፣ ስለ ፍቅራቸው የእጅ መንሻ ሰጥተዋቸዋል፤ ከአጠገባቸው አስቀምጠው እንደ እርሳቸው አንግሰዋቸዋል፤ የንጉሥ ባለቤት፣ የንጉሥ እናት፣ የንጉሥ አያት፣ ራሳቸውም ንግሥት ናቸው፡፡  በማያረጅ  ብራና ጎላ ብለው ተጽፈዋል፣ በማይጠፋ ቀለም ረቀቅ ብለው ተቀርጸዋል። በዙፋን ላይ የተዋቡ እመቤት፣ በችሎት ላይ ፍትሕ አዋቂ ንግሥት፣ በማድ ቤቱ ጥንቅቅ ያሉ ሴት ናቸው። እንደ ንግሥት ይፈርዳሉ፣ እንደ እመቤት በክብር ይኖራሉ፣ እንደ መልካም ሴት የሴትነቱን ሙያ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በዙፋን ላይ ተቀምጠው ፍርድ እየሰጡ፣ በጓዳ ገብተው ያማረውን ጠጅ ይጥላሉ፣ ያስጥላሉ፣ በሀገሩ ወይን ተክለው ወይን እንደ ውኃ ይቀዳሉ፡፡

በዚያ ባማረ ቤተ መንግሥት  ረዘም ላለ ዓመታት እቴጌ ተሰኝተው ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል፣ የአባቶቻቸውን ታሪክ ጠብቀዋል፣ የራሳቸውንም የጎላ ታሪክ ሠርተዋል፣  ሥርዓት እንዳይፈርስ ለልጅ ቃል ኪዳን አውርሰዋል፡፡  ለቤተ መንግሥቱ ግርማ የሚመጥነውን፣ ለታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ የሚኾነውን፣ ለታላቅ ሕዝብ የሚበጀውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ የመሲህ ሰገድ በካፋ ባለቤት፣ የብርሃን ሰገድ ኢያሱ እናት፣ የአጼ ኢዮአስ አያት፣ የቋረዋ እመቤት፣ የጎንደሯ ልዕልት፣ ብልኋ  ንግሥት እቴጌ ምንትዋብ፡፡

መሲህ ሰገድ በካፋ የቋረኛዋን እመቤት ባማረው ቤተ መንግሥት ሞሽረው ባመጧቸው ጊዜ  ጎንደር እልል አለች፣ አብዝታም ተደሰተች፣ ለንግሥቷ ክብርን ሰጠች፣ ፍቅርን አደለች፣ ከፍ ከፍም አድርጋ አሞገሰች፣ ቅኔ እየተቀኘች ምሥጋናን አቀረበች።

ዓለም ባልሰለጠነበት፣ ሴቶች በሚናቁበት፣ በወንድ ሀሳብ እና ትዕዛዝ ብቻ በሚኖሩበት በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሴቶች ዘውድ ጭነው ሀገር ያሥተዳድሩ፣ ትውልድ ይመሩ ነበር።  እንደ ወንዶች ሁሉ ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ፣ በቀኝ እና በግራቸው መኳንንቱን እና መሳፍንቱን አስቀምጠው ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ ፍርዳቸውም ፍትሕ የመላበት፣ የእናትነት አንጀት የማይለይበት፣ ብልሃት የበዛበት ነበር፡፡

እቴጌ ምንትዋብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ሴት ነገሥታት መካከል አንደኛዋ ናቸው፡፡ በጎንደር ዘመን ስማቸው ከናኙ፣ በተዋበው ቤተ መንግሥት ኾነው እየተከበሩ እና እየተፈሩ ኢትዮጵያን ካሥተዳደሩ ነገሥታት መካከል እቴጌዋ በትልቁ ይነሳሉ፡፡ ስለ እርሳቸው የሚናገሩ የታሪክ አሻራዎች ዛሬም ድረስ በመናገሻዋ ከተማ መልተዋል፡፡ ከመናገሻዋ ከተማ ባሻገርም በሌሎች አካባቢዎች የእርሳቸው አሻራዎች በዝተዋል፡፡

አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በተሰኘው መጻሕፋቸው መሲህ ሰገድ በካፋ እቴጌ ምንትዋብን ከማግባታቸው አስቀድመው እቴጌ አዋልደን በቁርባን አግብተው ነበር፡፡ ነገር ግን  በሠርጋቸው ቀን  እቴጌዋ ባልታወቀ ምክንያት እንዳረፉ እና ሀዘን እንደኾነ ጽፈዋል።  ተክለጻድቅ መኩሪያም እቴጌ አዋልደ ሠርጉ ሳያልቅ ማለፋቸውን በታሪክ መጻሕፋቸው አስፍረዋል፡፡

መሲህ ሰገድ በካፋ ለአደን ወደ ቋራ በሄዱበት ወቅት በወባ በሽታ በመያዛቸው በአካባቢው ከነበሩት ባላባት ቤት ገብተው ከሕመማቸው እስኪያገግሙ ድረስ ሰነበቱ። ባረፉበት የባላባት ቤት ታስታምማቸው የነበረችውን ምንትዋብ የተባለችውን የባላባቱን ልጅ ወደ ቤተ መንግሥት ሲመለሱ ሽምግልና ልከው አዲስ ትዳር መሠረቱ  ይላሉ አሰግድ ተስፋዬ በታሪክ መጻሕፋቸው፡፡ እኒህ የባላባት ልጅ የተዋቡት እመቤት የመሲህ ሰገድ በካፋን ልብ ሰርቀዋልና ወደ ቤተ መንግሥት መጡ፡፡ አስቀድሞ ገና ደም ግባታቸው እና ውበታቸው ለንግሥና የተመረጠ እና የተዋበ ነበርና ዘውድ ጭነው ከባለቤታቸው ጋር  ተቀመጡ፡፡

ተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ በተሰኘው መጻሕፋቸው  አጼ በካፋ ለአደን ወይም ግዛት ለማየት ወደ ስናር ድንበር ሄደው ሳለ የወባ በሽታ ስለ ታመሙ ቋራ በባላባቱ ቤት ገብተው ተኙ። ንጉሥ መኾናቸውን ሳያውቅ ባላባቱ ተቀብሎ በቤቱ አስተኛቸው ይባላል። የባላባቱም ውበት ያላት ሴት ልጁ ስታስታምማቸው ሰነበተች። በዚያውም በታመሙበት ጊዜ ድኜ ጎንደር ስገባ ይህችን ልጅ አገባለሁ ብለው አሰቡ። እንዳሰቡትም ከሕመማቸው ድነው ጎንደር ሲገቡ መኳንንቶቻቸውን ልከው ወጣቷን አምጥተው በጎንደር ታላቅ ድግስ ተደግሶ በሠርግ አገቡ። እኝህም ሴት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የታወቁት ስመ ጥሩይቱ እቴጌ ምንትዋብ ናቸው። የክርስትና ስማቸው ወለተ ጊዮርጊስ የንግሥትነት ስማቸው ደግሞ ብርሃን ሞገሳ ይባላል  ብለው ጽፈዋል። በርግጥ  ብርሃን ሞገሳ የተሰኘው ስማቸው በቋራ እያሉም ውበታቸውን ያዩ ሁሉ ብርሃን ሞገሳ እያሉ ይጠሯቸው ነበር ይባላል፡፡

እቴጌይቱ በኋላ ብርሃን ሰገድ ተብለው የነገሡትን ኢያሱን ለበካፋ ወለዱላቸውና ታላቅ ደስታ ኾነ። የእቴጌ ምንትዋብ ዘር ከነገሥታቱ ዘር የሚመዘዝ እንደኾነ ተክለጻድቅ መኩሪያ ከትበዋል። እቴጌ ምንትዋብ በቤተ መንግሥቱም፣ በቤተ ክህነቱም በሕዝቡም ዘንድ የተከበሩ እና የተፈሩ ነበሩ ይባላል። ከባለቤታቸው ከአጼ በከፋ ጀምሮ ይልቁንም በልጃቸው በቋረኛ ኢያሱ በልጅ ልጃቸው በኢዮአስ ዘመን ሁሉ ከዚያም እስከ ተፈጻሚተ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ ዘመን ሲኖሩ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሙሉ ሥልጣን የያዙ እንደነበሩ ይነገራል።

የቋራዋ እመቤት እቴጌ ምንትዋብ ባለቤታቸው በመስከረም 1723 እንደሞቱ የስምንት ዓመት ልጃቸው አቤቶ ኢያሱ  የንጉሠ ነገሥት አልጋወራሽነቱን አረጋገጡ። ወደ መሀል ግምብ ገብተው ነገሥታቱ ሲሞቱ የሚለበሰውን የሀዘን ልብስ ከልጃቸው ጋር ለበሱ። የአጼ በካፋን አስከሬን በአደናግር በር በኩል ወደ አደባባይ ተክለ ሃይማኖት ሄዶ እንዲቀበር አደረጉ።

በንጉሠ ነገሥቱ ሞት ለሕዝቡ “የሞትን እኛ ያለንም እኛ ” የሚለውን አዋጅ ድብ አንበሳ ነጋሪት እየተጎሰመ የአቤቶ  ኢያሱ መንገሥ እንዲታወጅ አደረጉ። በዚህ ዓመትም ታኅሳስ ወር ብርሃን ሠገድ ኢያሱ ዳግማዊ ተብለው የንግሥና ሥርዓት ሲፈጸም እቴጌ ምንትዋብ ብርሃን ሞገሳ ተብለው ንግሥተ  ንገሥታት ተብለው ነገሡ። ብርሃን ሰገድ ሞገሳም ወንድማቸውን ራስ  ወልደ ልዑልን በራስ ቢትወደድነት ማዕረግ ሾመው ሀገሪቱን በበላይነት መምራት ጀመሩ  ብለው ጽፈዋል አሰግድ፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ ደግሞ የእቴጌ ምንትዋብ ባለቤት አጼ በካፋ ሲያልፉ ልጃቸው ኢያሱ ስመ መንግሥታቸው ብርሃን ሰገድ ተብሎ ነገሡ። በእናታቸውም የቋራ ተወላጅ ስለኾኑ ቋረኛው ኢያሱ እየተባሉ ይጠራሉ። ለአድያም ሰገድ ኢያሱም ሁለተኛ በመኾናቸው ዳግማዊ ኢያሱ ይባላሉ። በነገሡ ጊዜ እድሜያቸው ያልበሰለ ስለኾነ በነገሡበት ቀን እናታቸው እቴጌ ምንትዋብ እንደ ንግሥት  ዘውድ ጭነው በሞግዚትነት ነገሡ። እቴጌም ኀይለኛ እና ብልህ ስለ ነበሩ ከልጃቸው ከንጉሡ ይልቅ የእርሳቸው ኀይል እና ሥልጣን የገነነ ነበር ብለዋል፡፡
እቴጌ ምንትዋብ ውበታቸው የሚደነቅ፣ ሲያዩያቸው የሚያሳሳ፣ የሚያስገርሙ እንደነበር ይነገራል። እኒያ ንግሥት ያማረውን ዘውድ ደፍተው፣ በሀር ዝምዝም የተዋበውን፣ በአልማዝና በወርቅ ያሸበረቀውን፣ ከግርማ ላይ ግርማ የሚጨምረውን ካባቸውን ደርበው፣ በቀኝ እና በግራ፣ በፊትና በኋላ ታጅበው፣ እጅ እየተነሳላቸው፣ የወርቅ ምንጣፍ እየተነጠፈላቸው፣ የወርቅ ጫማ ተጫምተው እየተዘናከቱ  ሲወጡ ሲታዩ ውበታቸው ግሩም ድንቅ ይባል ነበር። ያያቸው ሁሉ ይገረምባቸዋል፣ ደስም ይሰኝባቸዋል፣ የውበታቸውን ነገር እያየ ያደንቃል ይባላል።

የእርሳቸውን ውበት እና ደም ግባት ያዩ የመናገሻዋ የጎንደር ነዋሪዎችም በቅኔ አወደሷቸው።
“አሁን ወጣች ጀምበር
ተደብቃ ነበር።
ደስ ይበልህ ጎንደር” እያለ አደነቃቸው። ውበታቸውን ከጀምበር ጋር እያነጻጸሩ፣ ተደብቀው የኖሩ ጀምበር፣ ብርሃን፣ የውበት ገምቦ፣ የደም ግባት መለኪያ መኾናቸውን አወደሷቸው። አስታዋይነታቸው፣ ብልሃታቸው፣ ሥርዓት አዋቂነታቸው፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የነበራቸው ጥበብም የሚደነቅ እንደኾነ ይነገርላቸዋል።  በዚህ ዘመን ችግሮችን በዲፖሎማሲያዊ መንገድ መፍታት የሚለው ጥበብ በእርሳቸው ዘመን በእጅጉ ይተገበር ነበር ይባላል፡፡

እቴጌ በዘመናቸው  አድባራትን በማስደበር፣ ገደማትን በማስገደም፣ የተዋቡ አብያተ መንግሥታትን በማሳነጽ ይታወቃሉ። ጥበብ የተቸራቸው ብልህ ንግሥት፣ ዘመናት ሲተካኩ ስማቸው የሚነሳ፣ ታሪካቸው የሚታወስ፣ ትውልድ ሁሉ አርዓያ የሚያደርጋቸው ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተዋል።   በመናገሻው ግቢው ቤተ መንግሥት አስገንብተዋል። ከእርሳቸው አስቀድመው የነበሩ ነገሥታትም በዚሁ ታላቅ ቤተ መንግሥት ቅጽር ግቢ አብያተ መንግሥታትን አሠርተዋል።

በታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጽር የተሠራው የእቴጌ ምንትዋብ ቤተ መንግሥት በቀይ ድንጋይ፣ በኖራ፣ በጎንደር መስቀል፣ በቤተ ክርስቲያን መንበር እና በሌሎች ውብ ማስጌጫዎች የተዋበ ነው ይባልለታል።  እቴጌ ምንትዋብ ከታላቁ ቤተ መንግሥት ባሻገር  በስተ ምዕራብ በኩል በሚገኘው ውብ ሥፍራም የደብረ ጸሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን እና የራሳቸውን ቤተ መንግሥት፣ በደምቢያ ቸመራ ቁስቋምን፣ የናርጋ ሥላሴ ገዳም  እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ማሠራታቸውን ታሪክ ይናገራል፡፡ ገዳማትን አስገድመዋል፡፡   በአለፋ የሚገኘውን የሞገዳ ቤተ መንግሥትም አሳድሰዋል ሲሉ አሰግድ ጽፈዋል።  ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ደግሞ የክብራን ገብርኤልን ከልጃቸው ጋር እርሳቸው እንዳሠሩት ጽፈዋል።  እቴጌ ምንትዋብ በተለይም በጎንደር የሚያስደንቀውን የቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሢያሠሩ  ሺህ ወቄት ወርቅ ከራሳቸው እንዳወጡ ይኸም የማይበቃ ቢኾን የጣታቸውን ቀለበት አውልቀው እንደሰጡ ይነገራል።

እኒህ ጥበብ የተቸራቸው ንግሥት በቤተ መንግሥቱ፣ በቤተ ክህነቱ የተዋጣላቸው ናቸው። በሴትነቱም አንቱ የተሰኙ ሴት ናቸው። ሙያ እና ሴትነት ከእርሳቸው በላይ ላሳር የሚባልላቸው፣ ሴትነትን የሚያስተምሩ፣ በሙያ የተራቀቁ ስንዱ እመቤት ናቸው። በጎንደር አብያተ መንግሥታት ውስጥ ቀጭን ፈታዮች እና ወይዛዝርት ግንብ እየተባለ የሚጠራ ሴቶችን ሙያ ሲያሰለጥኑበት የነበረ ያማረ ሕንጻ አለ። በዚህ ቦታ ለቤተ መንግሥት እና ለአብያተ ክርስቲያናት የሚያስፈልጉ አልባሳት እና ሌሎች መገልገያዎች ይሠራበት እንደነበር ይነገራል። የከተማዋን ወይዛዝርትም ሙያ ያስተምሩበት ነበር። ቀጭን ይፈተላል፤ ለነገሥታቱ፣ ለመኳንንቱ፣ ለመሳፍንቱ፣ ለሊቃውንቱ፣ ለወይዛዝርቱ ፣ ለጎበዛዝቱ ክብር እና ማዕረግ የተገባው ይሠራበታል፡፡

የዶሮ ወጥ 12 ብልት የተከፈለችበት፣   በቅመም ተሠርታ የቀረበችበት በዚሁ ስፍራ በእርሳቸው ዘመን  እንደኾነም ይነገራል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚወደደው እና አምሮ የሚሠራው ይህ ውብ አሠራር  ሲነሳ የእርሳቸው ሴትነት አብሮ ይነሳል። ጥርስ ንቅሳት እና ሌሎች መዋቢያዎችንም አስተምረዋል፡፡ እቴጌ በዚያ ዘመን ብቻ አይደለም በዚህ ዘመን ላሉ ሴቶችም አርዓያ የሚኾኑ ብርቱ ንግሥት ናቸው፡፡  ከባለቤታቸው፣ ከልጃቸው እና ከልጅ ልጃቸው ጋር እስከ 47 ዓመታት ድረስ በሥልጣን ላይ እንደነበሩ የሚነገርላቸው እቴጌ ምንትዋብ ብልህነታቸው እና አስታዋይነታቸው ለትውልድ መማሪያ መጽሐፍ ነው ይባልላቸዋል፡፡

ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በተሰኘው መጽሐፋቸው  ባለዝና ፣ በጎንደር ዘመን ስማቸውን በወርቅ ቀለም ያጻፉ፣ ንቁ፣ ኀይለኛ፣ ተራማጅና ጠንካራ መንፈሳዊ ነበሩ ይሏቸዋል፡፡ እርሳቸው ደፋር እና የውሳኔ ሰው እንደነበሩም ይነገራል፡፡ እኒህ ታላቅ እመቤት፣ ብልህ ንግሥት በዘመናቸው አያሌ ታሪኮችን ሠርተው፣ ለትውልድ የሚበቃ አርዓያነት አስቀምጠው ራሳቸው ባሠሯት ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን በጾምና በጸሎት ተወስነው አረፉ፡፡ ያረፉበት ዘመንም ግንቦት 26 1765 ዓ.ም እንደኾነ ታምራት ጽፈዋል፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያም እቴጌ በቁስቋም በጾም እና  በጸሎት እንደቆዩ በዚያው ማረፋቸውን ጽፈዋል፡፡ በዚህችው ያማረች እና የተዋበች ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ክብር ተቀበሩ ብለዋል፡፡ 

ታላቋ ንግሥት በሠሯቸው ታላላቅ ታሪኮች ይታወሳሉ፤  በትውልድ ልብ ውስጥ ይኖራሉ፤ ስለ ሠሩት ታሪክ ይወደሳሉ ይሞገሳሉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ
Next articleበሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የአንድ ኮር ስታፍ አባላት ለተማሪዎች ዩኒፎርም እና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።