“ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ

27

ደሴ: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2016 ዓ.ም ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል። በምክክር መድረኩ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የትምህርት ሥራ ቅንጅታዊ አሠራር የሚፈልግ ነው ብለዋል። ዓመቱን ሙሉ የተለፋበት የትምህርት ሥራ ፍሬ እንዲያፈራ እና አጨራረሱ እንዲያምር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል በአጠቃላይ ከ10 ሺህ 97ዐ በላይ ተማሪዎች ፈተና ለመውሰድ መመዝገባቸውን ከከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን ለመፈተን ከ3 ሺህ 190 በላይ ተማሪዎች መዘጋጀታቸውም ተጠቅሷል።

የመምህር አካለወልድ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ወንድአንተ ደምስ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 556 ተማሪዎችን ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎችን እንደሚያስፈትኑ ነግረውናል። ተማሪዎች በዕውቀት ብቁ እንዲኾኑ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን፣ በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲኾኑ ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለተማሪዎች ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባል ኤንስፔክተር አለባቸው መለሰ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካሉ በቅንጂት እንደሚሠራ ገልጸው፤ በፈተና ወቅት ተማሪዎች ለጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ተማሪዎች ከባለፈው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት መሠራቱን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ይከሰቱ የነበሩ የፈተና ሥርዓት ግድፈቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ እና ከአሁናዊ የሰላም ሁኔታ አንፃር ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ነው ያብራሩት። ለተማሪዎች በተሰጠው የሞዴል ፈተናም አበረታች ውጤት ስለማየታቸው ነው የተናገሩት። የ6ኛ ክፍል ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሰጠቱ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰሜን ወሎ ዞን መሪዎች ሰላምን በማጽናት ዙሪያ እየመከሩ ነው።
Next article“የተሰናዱ እመቤት፤ የተዋቡ ንግሥት”