
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የቀድሞው የደቡብ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የአማካሪ ቦርድ አባል አባተ ኪሾ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ጎልተው የሚታዩ እና ለግጭት መንስኤ የኾኑ ችግሮች በውይይት በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማምጣት ለዜጎች እፎይታን የሚሰጥ መኾኑንም ነው የተናገሩት። በመኾኑም ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው ይገባል ነው ያሉት።
ባለድርሻ አካላት በተጨባጭ የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚያውቁ እና በአዕምሮ ተዘጋጅተው የውይይት መድረክ የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኾናቸውን ጠቁመዋል። የወከሏቸውም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሃይማኖትን፣ ፆታን፣ ዕድሜን እና መሰል ልዩነቶችን ያማከለ በመኾኑ ለውይይቱ ጥሩ ግብዓት የሚኾኑ አጀንዳዎች እንደሚሠጡ አመላክተዋል።
በኮሚሽኑ በኩል የምክክር ሂደቱን በማከናወን ተጨባጭ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር ማስተባበር መኾኑን አስታውሰው ለምክክሩ ስኬት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የምንመኛትን ሰላማዊ ሀገር ለማግኘት የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል። ኮሚሽኑ በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚያከናውነውን ተግባር በመደገፍ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምክክሩ የሚጠበቀው ውጤት እንዲገኝ የሁሉም ባለድርሻ ተሳትፎ አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመው ሥራውን በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያስፈጽሙት ሳይኾን ሰፊ ተሳትፎ የሚፈልግ መኾኑን አመላክተዋል። የምክክር ኮሚሽኑ አማካሪ ቦርድም ለኮሚሽኑ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የተናገሩት አቶ አባተ የሚደረገው የሃሳብ ድጋፍ ለኮሚሽኑ ትልቅ እገዛ መኾኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ሂደቱን ሥርዓት ባለው መልኩ በማስኬድ በሁለት ዓመታት ቆይታው መሠረታዊ ነገሮች አከናውኗል ነው ያሉት። ኢፕድ እንደዘገበው በምክክሩ ተስፋ ያደረገውን የኅብረተሰብ ክፍልም በቅርበት ለመድረስ የሚያስችለውን የመጀመሪያውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ጊዜ ኮሚሽኑ በጥሩ መንገድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ለምክክሩ ስኬታማነትም ኅብረተሰቡ እምነት የጣለባቸው የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!