
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እየተሠሩ ያሉ የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት እና የአንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በዞኑ ከፍተኛ የሥራ መሪዎች ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ እና የቃብትያ ሁመራ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። የቃብትያ ሁመራ ወረዳ አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ የነገውን ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመቅረጽ የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በወረዳው እየተገነባ ነው ብለዋል።
በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በሀገር ወዳድ ዲያስፓራዎች የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በወረዳው መሠራታቸውን ያነሱት አሥተዳዳሪው በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በብአከር ከተማ የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት እና በአዲኽርዲ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እያስገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሕጻናትን ከስር ኮትኩቶ ለማሳደግ ትምህርት ቤቱ ወሳኝ መኾኑን አንስተው ሆስፒታሉም የብዙዎችን ሕይዎት ከህልፈት እንደሚታደግ ጠቁመዋል።
ለአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤቱ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ እና ለሆስፒታሉ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልግ መኾኑን ጠቁመዋል። እንደዚህ ዓይነት የማኅበረሰብ መገልገያዎችን ዞኑ ምንም እንኳን በጀት ባይኖረውም ኅብረተሰቡን በማስተባበር እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማሳተፍ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ለግንባታው መጠናቀቅ የሁሉም ሕዝብ ርብርብ የሚያስፈልግ መኾኑን ጠቁመው ማኅበረሰቡ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች አሁንም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ያገኙትን ነፃነት በማስቀጠል የልማት ሥራዎችን ኅብረተሰቡ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማሳተፍ ዞኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነ የገለጹት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው። “ያለምንም በጀት ታሪክ የሚያስታውሰው ሥራ እየተሠራ ነው” ብለዋል።
የአፀደ ሕጻናት ትምህርት ቤቱ ሕጻናት የሀገራቸውን ታሪክ አውቀው እና ተረድተው ነገ ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ጎዳና እንዲያሻግሩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት። የሆስፒታል ግንባታውም እናቶችን ከተለያዩ ችግሮች የሚታደግ እና ሕጻናት በተለያዩ ወረርሽኝ በሽታዎች ተጠቂ እንዳይኾኑ የሚያገለግል በመኾኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀው ወደ ሥራ ማስገባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ለመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ መሳካት የሁሉም እርብርብ የሚያስፈልግ መኾኑን ጠቁመው የአካባቢው ማኅበረሰብ ብሎም በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!