ረጃጅም ሰልፎችንና ተጠጋግቶ በታክሲ መሄድን በማስቀረት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ይከላከሉ!

154

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የእግር ጉዞ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን እንግታ፣ ጤናችንም እንጠብቅ!

የእግር ጉዞ ማድረግ ካሎሪን በማቃጠል ክብደታችን እንዲቀንስም ሆነ ባለበት እንዲረጋ ያደርጋል፡፡ በቀን 30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ ልባችን እንዲጠነክርም የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ልምድ ቀጥሎ ወደ ሳምንት ከዘለቀ ደግሞ ከልብ ጋር ተያያዥነት ባለው በሽታ የመያዝ እድልን በ19 በመቶ እንደሚቀንስ የጤና ምክረ ሀሳቦች ያስገነዝባሉ፡፡
ጤናማ ሕይወትን ከማስቀጠል ጀምሮ በርካታ ጥቅሞች ያሉት የእግር ጉዞ በዚህ ጊዜ ከተጋረጠብን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እራስንና ሕዝብን ለመታደግ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

በእግር መጓዝ በጠነከረ የጉንፋንም ሆነ የኢንፍሉዌንዛ (ፍሉ) በሽታ የመያዝ ዕድልን ሊቀንስ ይችላል፡፡ የፍሉ ወረርሽኝን በተመለከተ በአንድ ወቅት 1 ሺህ ጎልማሶችን በማሳተፍ በተሠራ ጥናት በመካከለኛ ፍጥነት በቀን ከ30 እስከ 45 ደቂቃ የእግር ጉዞ ያደረጉት በ43 ከመቶ ዝቅተኛ ህመም እንደተከሰተባቸው ተመላክቷል፡፡ እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ጎልማሶች ጋር ሲነጻጸርም በበሽታው ቢያዙም እንኳ የሚታዩባቸው የበሽታው ምልክቶች ቀንሰው ተገኝተዋል፡፡

እንደ ጉንፋንና ተዛማጅ በሽታዎች በቫይረስ የሚመጣው ኮሮና ቫይረስም በፍጥነት ተዛማችና መድኃኒት አልባ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ከጥንቃቄዎች መካከልም ረጃጅም ሰልፎችንና ጥግግትን ማስወገድ አንዱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመዘንጋት አለያም ችላ በማለት ይመስላል በተሽከርካሪዎች ለመሳፈርና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ሰዎች በረጃጅም ሰልፎች ተጠጋግተው ይስተዋላሉ፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አዘውትሮ በሳሙና በመታጠብ የእጅን ንጽህና ከመጠበቅ ባለፈ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍና መሰባሰብን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡

በተለይም በመጠጋጋትና በመነካካት የሚከሰትን በበሽታው የመያዝ ስጋት ለመቀነስ የእግር ወይም የብስክሌት ጉዞን ምርጫ ማድረግ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ይታመናል፡፡ በጤና ባለሙዎች የተላለፈውን ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ ያህል ርቀት ጠብቆ መቆምም ሌላው አማራጭ ነው፡፡

አሁን ላይ በከተሞቻችን እያስተዋልነው ያለው መዘናጋት ግን መፍትሔ የሚያሻው ነው፡፡ ሰዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ “ርቀትዎን ይጠብቁ” የሚለውን መርህ በጣሰ መልኩ ሆኗል፡፡ ረጃጅም ሰልፎቹ ጤናን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ በተጨናነቀ ሁኔታ በሕዝብ መጓጓዣዎች መገልገሉም አልተገታም፡፡ ስብሰባዎችም ሙሉ በሙሉ ተገትተዋል ለማለት ያዳግታል፡፡ እናም መዘናጋቱና ችላ ማለቱ ይብቃንና እንጠንቀቅ፣ እራሳችንና ሕዝቡንም ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንጠብቅ፡፡

እስከ ትናንት መጋቢት 10/2012 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ዘጠኝ ደርሷል፡፡ በዓለማችን ደግሞ በቫይረሱ የተነሳ 10 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ነው የተነገረው፡፡ ከ244 ሺህ 500 የሚልቁት ደግሞ በቫይረሱ እንደተያዙ ነው እየተዘገበ የሚገኘው፡፡ ለዚህም ነው እንጠንቀቅ፤ ጤናችንም እንጠብቅ እያልን ያለነው፡፡

በኪሩቤል ተሾመ
ፎቶ፡– በአስማማው በቀለ

Previous articleበታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽ ተማጽኖ እና የጀርመን አጸፋ!
Next articleሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችን በከፊል ዘጋ፡፡