
አዲስ አበባ: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፋዊ የሲቪል አቬሽን ደኅንነት ኦዲት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የአቬሽን ደኅንነት ኦዲቱ ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቬየሽን ድርጅቶች ጋር በጥምረት የሚከናወን ነው ተብሏል። የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ሲሳይ ቶላ በአየር መንገዱ ውስጥ ደኅንነት እና ምቾት እንዲመጣ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለድርሻ አካለት ጋር በመተባበር እና ጠንካራ ኔትወርክ በመዘርጋት የሚሠራ ግንባር ቀደም የአቬየሽን ደኅንነት ተቋም ኾኗል ነው ያሉት። በተለያዩ ጊዜያት ራሱን እያጠናከረ መጥቶ አሁን “የአቬየሽን ደኅንነቱ ጠንካራ እና ችግሮች የማይጥሉት ተቋም ኾኗል” ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጄኔራሉ።
አየር መንገዱ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል አየር ማረፊያ እየገነባ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀኔራሉ እኛም በዚህ ልክ ራሳቻንን እያደራጀን ነው ብለዋል። የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት የሲቪል አቬየሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ በበኩላቸው ብሔራዊ መረጃ ደኅንነት የሰው ኃይል በማሠልጠን እና በቂ መሳሪያዎችን በማሳማራት የአቬየሽን ደኅንነትን ለማስጠበቅ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል። በአሁኑ ሰዓትም ከ2 ሽህ በላይ ብቁ ሠራተኞችን አሰማርቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በፀጥታው ዘርፍ ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን ቀድሞ በመለየት እና በመከላከል እየሠራ ነው ብለዋል ኀላፊው። በአዳዲስ ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ታግዞ ሥራውን እያቀላጠፈ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!