
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2002 ዓ.ም የግንባታ ሂደቱ የተጀመረው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ደረጃን ባሟላ መልኩ ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በመበጀት ከተቋራጩ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ጋር ውል ገብቶ እየተሠራ ነው።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ የባሕር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎችን ጨምሮ ከካፍ ደረጃ በላይ ተጨማሪ መሠረታዊ የደረጃ ማሟያ ግንባታዎች እና ባለአምስት ኮከብ የውስጥ ቁሶች እንዲሟሉለት ተደርጎ በከፍተኛ ወጪ፣ በጥራት እና በጥንቃቄ እየተገነባ ነው ብለዋል።
አሁን ባለው የግንባታ ፍጥነት በጥር ወር የካፍ ውድድሮችን ለማስጀመር እንዲያስችል እየተሠራ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። 47 ሺህ ወንበሮች ጥሬ ዕቃቸው ከውጭ ገብቶ በሀገር ውስጥ መመረት መጀመራቸውን እና ለቪ.አይ.ፒ የሚያገለግሉ 4 ሺህ 5 መቶ ወንበሮች ከስፔን እና ከቱርክ ተመርተው እንዲገቡ በኮንትራክተሩ በኩል ስምምነት ተወስዷል ብለዋል።
አቶ እርዚቅ የፌደራል መንግሥት የዶላር ምንዛሪ ዕጥረት ሳይገጥመን ግንባታው በፍጥነት እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እገዛ እያደረገልን ስለሆነ ከልብ እናመሠግናለን ብለዋል። አያይዘውም የፌደራል መንግሥት ፌዴሬሽኖችን እና አጋር አካላትን በማሥተባበር የስታዲየሙን ጣራ በማልበስ፣ የመለማመጃ ሜዳዎች የሩጫ መም (Track) ማንጠፍ፣ የቤት ውስጥ ውድድሮች (Indoor games) ማካሄጃ ስታዲየም በመገንባት እና የመወዳደሪያ የስፖርት ቁሶችን (Equipment) ድጋፍ በማድረግ እንዲያግዘን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኤምኤች ኢንጅነሪንግ የአማካሪዎች ቡድን መሪ ኢንጅነር እስክንድር ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደት በጥራት እና በፍጥነት እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ባለው የግንባታ ሂደት እስከ ጥር 2017 ዓ.ም ድረስ በገባነው ውል መሠረት የካፍ ውድድሮችን ለማካሄድ ከሚያስችል በላይ አጠናቅቀን እናስረክባለን ብለዋል።
በተለይ የሜዳ ሥራ ላይ የፊፋ ፈቃድ ያለው የፈረንሳዩ ግሪጎሪ ተቋራጭ ድርጅት በጥራት እና በፍጥነት ሥራውን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሲጠናቀቅ 52 ሺ ተመልካቾች የሚይዝ ሲሆን፤ 29 የኦሎምፒክ ስፖርቶችን በተመሳሳይ ሰዓት ማወዳደር የሚችል የኦሎምፒክ ስታዲየም እንደሚሆን የስታዲየሙ ፕላን እንደሚያሳይ ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!