
👉 እቴጌዋ በ«ጎማ»
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እቴጌ ምንትዋብ 1700 ዓ.ም አካባቢ ጎንደር ቋራ ውስጥ ተወለዱ፡፡ በዘመናቸው በዓጼ ልብነ ድንግል ጊዜ እንደነበሩት እንደ አጼ በዕደ ማርያም ባለቤት እቴጌ እሌኒ እና እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ በቤተ መንግሥቱም በሕዝቡም ዘንድ የተከበሩ እና የተፈሩ ነበሩ። እቴጌይቱ ከባለቤታቸው ከአጼ በካፋ ጀምሮ በልጃቸው በቋረኛ እያሱ እና በልጅ ልጃቸው በኢዮአስ ዘመን 40 ዓመታት ሙሉ ሥልጣን ይዘው ቆይተዋል፡፡
ተክለጻዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳተቱት የእቴጌ ምንትዋብ የክርስትና ስም ወለተጊዮርጊስ ይባላል፡፡የዙፋን ስማቸው ደግሞ ብርሃን ሞገስ ይባላል።
እቴጌ ምንትዋብ “ንግሥት” ተብለው የወርቅ አክሊል ደፍተው እና የወርቅ ጫማ ተጫምተው «ጎማ» በሚል መጠሪያ በሚታወቀው በቅሏቸው ላይ ተቀምጠው ወደ አደባባይ በወጡ ጊዜ ሕዝቡ የሚከተለውን ዘፈን በመዝፈን የደስታቸው ተካፋይ ኾነላቸው።
አሁን ወጣች ጀምበር ፣
ወጣች ጀምበር፣
ተሸሽጋ ነበር።
ፋንታውን እንግዳ “ታሪካዊ መዝገበ ሰብ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ እቴጌ ምንትዋብ የኢትዮጵያን ሰላም አስጠብቀዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ አብያተ – ክርስቲያናትን ማሠራታቸውንን ጠቅሰዋል። ካሠሯቸው አብያተ-ክርስቲያን መካከል የጎንደር ቁስቋም፣ በጣና ሐይቅ፣ በደቅ ደሴት ላይ የሚገኘውን ናጋ ሥላሴ እና በጎንደር ከተማ ያለው መጥምቁ ዮሐንስ ይጠቀሳሉ። ጣና ሐይቅ የሚገኘውን የደጋ እጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያንንም አሳድሰዋል።
ተክለጻዲቅ መኩሪያም እቴጌ ምንትዋብ በጎንደር የሚያስደንቀውን የቅድስት ቁስቋምን ቤተ ክርስቲያን በዘመናቸው ማሠራታቸውን ጽፈውላቸዋል፡፡
እቴጌ ምንትዋብ ለሙያዎች ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡ ስለነበር ሴቶችን አሠባሥበው ሙያ ያስተምሩ ነበር። አሁንም ድረስ የእቴጌ ምንትዋብ ሙያ የሴት ልጅ ልኬት ኾኖ ያገለግላል።
“ታሪክ ወንግሥት ብርሃን ሞገሳ” የሚል አርስት በተሰጠው የእቴጌ ምንትዋብ ዜና መዋዕል እንደሰፈረው ራሳቸው ባሠሯት ቁስቋም ማሪያም ተጠግተው ለሚማሩ ተማሪዎች ትምህርቱን ለማበረታታት ይደግፉ ነበር ተብሏል፡፡
የዓባይ ወንዝን ምንጭ ለመፈለግ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ እቴጌ ምንትዋብ ምን ያህል በወቅቱ የሚፈሩ የሚከበሩ እና በጥበብ ወዳድነታቸው የሚደነቁ መኾናቸውን አወድሶ አስፍሯል።
እቴጌ ምንትዋብ በመሪነት ብቃታቸው ከተመሰከረላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች አንዷ የኾኑት የአጼ በካፋ ባለቤት፣ የአጼ ኢያሱ ዳግማዊ (የቋረኛ ኢያሱ) እናትና የአጼ ኢዮአስ አያት እቴጌ ምንትዋብ ብርሃን ሞገሳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚህ ሳምንት 1765 ዓ.ም ነበር።
👉የሰብዓዊ መብት ታጋዩ ኬኔዲ
አሜሪካውያን በጣም ከሚወዷቸው ፕሬዚዳንቶች አንደኛው ጆን ፊዝጀራልድ ኬኔዲ ነበሩ፡፡ የኬኔዲ አባት አንድ ቀን ከልጆቻቸው አንዱ ፕሬዝዳንት እንደሚኾን ተስፋ ነበራቸው፤ እሱም ኬኔዲ ነበር፡፡
ኬኔዲ በብላቴና ዘመኑ በማሳቹሴትስ ውስጥ ለሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ በመጫወት አደገ፡፡
ወጣቱ ኬኔዲ ሀገሩን በወታደርነት መስክም አገልግሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ1943 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአሜሪካ የባሕር ኃይል ውስጥ በማገልገል ላይ እያለ እርሱ የነበረበት ጀልባ አደጋ አጋጠመው፡፡
የመዋኛ ጃኬት የሌላቸው ባሕር ኀይሎች የዓሳ ሲሳይ ኾኑ፡፡ ኬኔዲ “ቆቅ” ነበርና የደኅንነት መጠበቂያ ካላቸው ወታደሮች የአንዱን ጃኬት ጥርሱን ነክሶ በመያዝ ሕይዎቱን አተረፈ፡፡
ኬኔዲ ከውትድርናው በተመለሱ ማግሥት ሴናተር ከኾኑ ብዙም ሳይቆይ በ1953 ዣክሊን ቡቪየርን አገቡ።
በ1960 ደግሞ የማሳቹሴትስን ሕዝብ ወክለው በተወካዮች ምክር ቤት እና በአሜሪካ ሴኔት ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረዋል፡፡ ታዲያ በወቅቱ የሪፐብሊካኑን ተፎካካሪ ሪቻርድ ኤም ኒክሰንን አሸነፉ ።
እ.ኤ.አ. ጆን ኤፍ ኬኔዲ በ1960 በእድሜ ትንሹ 35ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት በመኾን ተመረጡ፡፡
ኬኔዲ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የአሜሪካ ዜጎች ሁሉ የቆዳቸው ቀለም እና የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ታግለው አስከብረዋል፡፡ በሂደትም ለሁሉም ዜጎች የእኩልነትን መብት የሚያጎናጽፈው መብት ሕግ ኾኖ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ነጭ እና ጥቁር ተማሪዎች በአንድ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ለማስቻል ታግለው እውን አድርገዋል፡፡
ኬኔዲ ወደ ሥልጣን በመጡበት ዕለት ባደረጉት ንግግር አሜሪካንን የተሻለች ሀገር ለማድረግ ዜጎች እንዲረዷቸው የጠየቁበት ንግግር ዛሬ ድረስ በታሪክ ይጠቀሳል፡፡ “ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይኾን እኔ ለሀገሬ ምን ላድርግላት ብለህ ራስህን ጠይቅ” በማለት መናገራቸውን ነው ናሽናል ጅኦግራፊ በድረ ገጹ ያሰፈረው፡፡
ታዲያ ታሪካዊ ክስተቱ የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ነበር። ይህ ታሪክም ኬኔዲ በድጋሚ ለመመረጥ እ.ኤ.አ ግንቦት 22/1963 ዳላስ ቴክሳስ ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር የቅስቀሳ ዘመቻ ላይ በነበሩበት ጊዜ የተፈጸመ ነበር፡፡ በቅስቀሳው ላይ የተኩስ ድምፅ ተሰማ። ፕሬዚዳንት ኬኔዲ አንገታቸው እና ጭንቅላታቸው ላይ ተመቱ፤ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም። በሰዓታት ውስጥም ምክትል ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን ፕሬዚዳንት ኾነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ።
👉ቮልስዋገን
ቮልስዋገን በጀርመንኛ ቋንቋ ‘የሕዝብ መኪና’ ማለት ነው። ይህ የሕዝብ መኪና (ቮልስዋገን) ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረተው በጀርመን ዶይቸ አርቤይትስ ከተማ ውስጥ ግንቦት 20 ቀን 1929 ነበር፡፡ ቮልስዋገን ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤት ሚገኘው ቮልፍስበርግ ከተማ ነው፡፡ ለዚች ከተማ መዘመን ኩባንያው ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር የሚመራው ናዚ መኪናዋ ከጀርመን ያውም ከናዚ አባል ውጭ የኾነ ግለሰብ መኪናዋን እንዳይጠቀም ከለከለ፡፡ እናም የመኪናዋ ሽያጭ ተገደበ፡፡
ቀስበቀስ የጀርመንን ርእዮተ ዓለም በሚደግፉ ሀገራት እንድትሸጥ በመፈቀዱ ሽያጯ አንሠራራ፡፡
እኤአ በ1945 ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸነፈች፤ ቮልስዋገንም ነጻ ወጣች፡፡ መኪናዋ በዓለም ገበያ መሸጥ በመጀመሩ ዝነኛ ብራንድ ኾና ተፈለገች፡፡
ጀርመን እና ቻይና እኤአ በ2016 በደረሱት ስምምነትም ቮልስዋገን በጀርመን እና በቻይና መሐንዲሶች በሁለትዮሽ እንድትመረትም ተወሰነ፤ እናም ቻይና አንዷ የቮልስዋገን አምራች ኾና ብቅ አለች፡፡ በመኾኑም ቮልስዋገን በቻይና ገበያ በስፋት ተቀባይነትን አገኘ፡፡
የቮልስዋገንን 40 በመቶ ድርሻ የወሰዱት የቻይና የተሸከርካሪ አምራች ጠበብቶች የቮልስዋገንን ሞዴል አሻሽለው በማቅረባቸው እነኾ ዛሬ ላይ በዓለም ትልልቅ ከተሞች ቮልስዋገን ተመራጭ መኪና ኾኗል፡፡
ቮልስዋገን ጀርመን ግንባር ቀደሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛው ትልቁ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ነው ሲል ያስነበበው ኮንሲዩመር ሪፖርት ነው፡፡
ይህች ቮልስዋገን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረተችው በዚህ ሳምንት ግንቦት 20 ቀን 1929 ነበር፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!