
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአጀንዳቸው ላይ እየመከሩ ነው፡፡
ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የወረዳ የኅብረተሰብ ተወካዮች ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት በትናንትናው እለት ተጠናቅቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማትና የማኅበራት ተወካዮች፣ የኅብረተሰብ ወኪሎች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ተሳትፈዋል።
አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ እንዲሁም የመፍትሔ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፡፡
በሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውንም ይመርጣሉ፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው በዛሬው እለት አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በከተማ ደረጃ አጀንዳቸው ላይ ምክክር እያደረጉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ሀገር አቀፍ የምክክር ሂደት ትናንት መጀመሩ ይታወቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!