
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአሜሪካን ሽምግልና የሚጠይቅ ሳይሆን ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ተነጋግረው የሚፈቱት መሆኑን የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል ተናገሩ፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የሕዳሴ ግድቡን፣ የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ እና ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ በዋሽንግተን ስለተካሄዱ ድርድሮች ተነጋግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ግብፅ በዋሽንግተን የተዘጋጀውን የስምምነት ሰነድ ለመፈረም ፈቃደኛ ብትሆንም ኢትዮጵያ እና ሱዳን እንዴት ፈቃደኛ ሊሆኑ እንዳልቻሉ በውይይታቸው አልሲሲ ለሜሪከል ነግረዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በድርድሩ እንድትስማማ እንዲያግዟቸውም ጠይቀዋቸዋል፡፡
መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ጊዜ ወስደው ለመምከር እና ከሕዝባቸው ጋር ለመወያየት መወሰናቸው ክፋት እንደሌለው ገልጸውላቸዋል፡፡ የአሜሪካ ሽምግልና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽም ሀገራቱ ጉዳዩን በራሳቸው ተነጋግረው መፍታት እንደሚችሉ ለአልሲሲ ነግረዋቸዋል፡፡
ጉዳዩ የሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት በመሆኑ በተፋሰሱ ሀገራት መድረክ ሊታይ ይገባዋል ብለው እንደሚያምኑ ነው ሜሪከል የገለጹት፡፡ ባለፉት ሳምንታት የግብፅ ባለሥልጣናት በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
በተለይም ወዳጅ ናቸው፣ ይደግፉኛል ወዳሏቸው ሀገራት በመሄድ ውትወታቸውን አጠናክረውት ነበር፡፡ አወንታዊ ምላሽ ስለማግኘታቸው ግን ፍንጭ አልሰጡም፡፡ ምናልባት በጎ ምላሽ ቢያገኙ ኖሮ ዝምታን ባልመረጡ ነበር፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ