ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት

30

ኮሚሽኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ከተማ አቀፍ ምክክርን አስጀመረ።

ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የምክክር ምዕራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት አስጀምሯል።

በዓደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተጀመረው ከተማ አቀፍ የምክክር ምዕራፍ የኅብረተሰብ ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሦስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ፣ የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በምክክር ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽር መስፍን አርዓያ (ፕ.ር) አካታችና አሳታፊ ወደሆነው የዝግጅት ምዕራፍ ማገባደጃ እንዲሁም የምክክር ሂደት መግቢያ እና አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ማብሰሪያ ሂደት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ፈተናዎቹ ሳይበግሩት ለብዙ ዓመታት ብዙዎች ሲመኙት የነበረውን መቀራረብንና መግባባትን ለማምጣት ቆርጦ ሥራውን እያከናወነ ለዚህ ደረጃ መብቃቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ እስካሁን በአስር ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከ1ሺ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን በማስመረጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ መሰብሰብ ሥራውን እንደጀመረ አክለዋል፡፡ በቀጣይ ልክ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉ የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስዳደር አጀንዳ እንደሚሰበስብ የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ በአማራና በትግራይ ክልሎች ደግሞ የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች ብዙ ተምሮ የተሻለ የሰላምና የእድገት ውርስ ይተዋል የሚል እምነት ኮሚሽኑ እንዳለውም አክለዋል፡፡ ከስብራት ሕይወት ወጥተን ወደ ተሻለ ሕይወት እንሸጋገር ዘንድ ወጣቱ ችግሩን በአጀንዳ ቀረፃ ጠብመንጃውን ወደ ሃሳብ መንጃና ማንሸራሸሪያ እንዲቀይር ኮሚሽኑ በትህትና ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የሀገራችን ችግር ወደ ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደት የሰላም በር በየትኛውም ቦታ ላሉ ወገኖች እንዲመቻች ጠንክሮ እንደሚሠራም ዋና ኮሚሽሩ አረጋግጠዋል፡፡ በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳውን በግልም ሆነ በጋራ ወደ ኮሚሽኑ ማምጣት እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ኮሚሽሩ ምክክሩ አካታች እንደሚሆንና ሂደቱም ግልፅና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንደሚከወን በንግግራቸው አረጋግጠዋል፡፡

የሀገራቸው ሰላም እና እድገት አሳስቧቸው የምክክሩ ሂደት እንዲሳካ ኮሚሽኑን እያገዙ ላሉ ሁሉ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ.ር) በኮሚሽኑ ስም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከር የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር.)
Next articleለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሀገር አቀፍ ፈተና በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጠ።