
ከሚሴ: ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ በሰላም እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የውይይት መድረክ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አሕመድ መሐመድ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠቱ በርካታ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትን ወደቀያቸው በሰላም እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። የማያግባቡ ችግሮችን በጠረንጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባሕልን ማዳበር ይገባልም ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ጥያቄዎች ሰላም እና ልማት በመኾናቸው በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር.) የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የአብሮነት እሴትን እና ባሕልን ማጎልበት የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል ብለዋል። በሁሉም አካባቢዎች ቀጣናዊ ትስስር በመፍጠር በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።
ዶክተር አሕመዲን አክለውም የውስጥ አንድነትን በማጠናከር በከንቲባ ችሎት እና በሌሎች የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ መፍቻ መንገዶች የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በትብብር መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በውይይት መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብቶች እና ሌሎች ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!