
ደሴ፡ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ጽዱ ኢትዮጵያን እንፍጠር” በሚል መርሐ ግብር በደሴ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። ” ጽዱ ኢትዮጵያን እንፍጠር ” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተደረገውን ጥሪ በመቀበል የደሴ ከተማ ሕዝብ እና የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር በጋራ በመኾን ከተማዋን አጽድተዋል።
በጽዳቱ ተሳታፊ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በደሴ ከተማ እየተሠሩ ባሉ የከተማ ማስዋብ ሥራዎች መደሰታቸውን ገልጸው ወደፊትም ለከተማዋ ውበት እና ጽዳት የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል ። በሀገር መከላከያ በኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ የ103ኛ ኮማንዶ ክፍለ ጦር የ5ኛ ሬጅመንት ዋና አዛዥ ሻለቃ ታሪኩ ሻሜቦ የመከላከያ ሠራዊቱ ሰላምን ከማስፈን በተጨማሪ በተለያዩ ልማቶችም ኅብረተሰቡን እያገዙ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ደሴ ከተማን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ውበት እንዲጠብቅ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናግረዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለጽዳት የወጣው ሕዝብ ከተማዋ በልማት ጎዳና ላይ እየተራመደች መኾኑን እና አስተማማኝ ሰላም በከተማዋ መኖሩን ማሳያ ነው ብለዋል።
የከተማዋ አስተማማኝ ሰላም በጸጥታ መዋቅሩ ብቻ የተረጋገጠ ሳይኾን የሕዝቡ ሰላም ወዳድ ሚናው የላቀ በመኾኑ እንደኾነ ገልጸዋል። በጽዳቱ ተሳታፊ የነበሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮነን( ዶ.ር) በደሴ ከተማ የተሠሩ የልማት እና የከተማ ማስዋብ ሥራዎች የሚበረታቱ መኾኑን በመጥቀስ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚካሄደው እንቅስቃሴ ከደሴ እና አካባቢው ጎን በመኾን እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!