“በቀጣይ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥባቸው አዳዲስ የፓርቲ መመሪያዎች ይሰጣሉ” አቶ ፍስሀ ደሳለኝ

37

ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀትና ዘርፍና የኢንስፔክሽን ዘርፍ የ10 ወራት የአፈጻጸም የግምገማና የፓርቲ መመሪያዎች የሥልጠና መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው። በዚህ መድረክ በባለፉት 10 ወራት የተከናወኑ የፓርቲ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና እነዚህን ችግሮች በጥበብ ለማለፍ የተወሰዱ የመፍትሔ አማራጮች ይቀርባሉ።

በቀጣይ 100 ቀናት በሚከናወኑ ተግባራት ላይም የአፈጻጸም እቅድ ትውውቅ ይደረጋል ተብሏል። የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ እንዳሉት በቀጣይ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥባቸው አዳዲስ የፓርቲ መመሪያዎች ይሰጣሉ ብለዋል። የፖለቲካ መሪዎች የሚመዘኑበት አዲስ የምዘና መመሪያ፣ የዲሲፕሊንን መመሪያና የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት፣ የኮር አመራሮች ምዘና ሥርዓትና የተተኪ መሪዎች ልየታ መመሪያዎች ይተዋወቃሉ ነው ያሉት።

ጠንካራ ተግባር የሚከናወንበት የቀጣይ 100 ቀናት እቅድ የመድረኩ ትኩረት መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። በጠንካራ አደረጃጀት፣ እቅድና በተግባር አፈጻጸም የማይመራ የፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ መኖር የለበትም ያሉት አቶ ፍስሀ በባለፉት ጊዜያት በፈተና ውስጥም ኾኖ የተከናወኑ ተግባራትን በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል።

በውይይቱም በብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ አፈጻጸም ሊያመጣ የሚችል ሀሳብ እንደሚንሸራሸርበት ነው የገለጹት። በፌዴራል ኢንስፔክሽንና ሥነ ምግባር ኮሚሽን የኢንስፔክሽን ዘርፍ ዋና ዳይሬክተር መብራቱ ጉግሳ እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የኢንስፔክሽን ዘርፍ ኀላፊ ሳቤላ ፈቃድ ጨምሮ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀትና የኢንስፔክሽን ዘርፍ ኀላፊዎች እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ ኃላፊዎች በግምገማና በሥልጠና መድረኩ ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕርዳር ከተማ ለመሠረተልማት ሥራዎች ውጤታማነት የማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡
Next articleለጽዳት የወጣው ሕዝብ ከተማዋ በልማት ጎዳና ላይ እየተራመደች መኾኑ እና አስተማማኝ ሰላም በከተማዋ መኖሩ ማሳያ እንደኾነ ተገለጸ፡፡