አሁን በሕዝብ የሚጨክነው ነጋዴ የእሱ መኖሪያው የት ነው?

152

“ወቅቱ የሕዝብ ወገንተኝነትን የምናውቅበት ነው፡፡” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ነጋዴዎች በአቋራጭ ለመበልጸግ ከማሰብ ተቆጥበው በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከማኅበረሰቡ ጎን እንዲቆሙ ከተማ አስተዳደሩ አሳስቧል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን ዛሬ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው የሚገኙ የቴክኒክ እና የትግበራ ቡድኖችን በማደራጀት ቫይረሱን ለመከላከል እየሠራ እንደሆነ ገልጧል፡፡ ስለ ኮሮና ቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳዎችን ለመሥራት በየሰፈሩ ያሉት ወጣቶችም በአደረጃጀቱ ተካትተው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውንም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አማረ ዓለሙ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡

የተቋቋሙት አደረጃጀቶች የጽዳት ዘመቻና ሕግ የማስከበር ሥራ በማከናወን እንዲሁም አቅመ ደካማ ዜጎች ቫይረሱን የሚከላከሉበት ዘዴ እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል ምክትል ከንቲባው፡፡ ግብረ ኃይሉ በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት ነው፡፡ የቅድመ መከላከል ሥራውን ለመሥራትም በሆቴሎች፣ መጠለያዎች፣ የጉብኝት ቦታዎች፣ በየውሮፕላን ማረፊያ እና ፋብሪካዎች በየቀኑ ልዩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አቶ ዓማረ ተናግረዋል፡፡ ወደ ባሕር ዳር የሚገቡ ሰዎች በተለይ የውጭ ዜጎች ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አግባብነት በሌለው መልኩ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ኃላፊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ላይ እርምጅ እንደሚወሰድ የገለጹት ምክትል ከንቲባው “አሁን በሕዝብ የሚጨክነው ነጋዴ የእሱ መኖሪያው የት ነው? መንግሥት የራሱን እርምጃ ለመውሰድ ወደኋላ ባይልም እንደዚህ አይነት ነጋዴዎች በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከማኅበረሰቡ ጎን ቢቆሙ ጥሩ ነው’’ ብለዋል፡፡ ስግብግብ ነጋዴዎች ቢኖሩም ከመንግሥት ጋር በመሆን ድጋፍ የሚያደርጉ ብዙ ነጋዴዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ወቅት የሕዝብ መገልገያ ተሽከርካሪዎች ትርፍ መጫን ማሰብ እንደሌለባቸው ያሳሰቡት ምክትል ከንቲባው ኅብረተሰቡም ለራሱ ብሎ መንግሥትን ሳይጠብቅ ደንብ ማክበር እና ማስከበር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳድሩ በቂ የማቆያ ቦታ ማዘጋጀቱንም አቶ ዓማረ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ጤና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማማው ሞገስ በሰጡት የጋራ መግለጫ የቫይረሱን ስርጭት ከወዲሁ ለመከላከል ለ17 የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በ1ለ5 ቡድን ተደራጅቶ በሽታውን በሚከላከልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እያደረገ መሆኑን አቶ አስማማው ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳድሩ “ሳተላይት” ከተሞችን ጨምሮ በተለይ ወጣቱ የማኅበረሰቡን ጽዳት እና ጤንነት እንዲጠብቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ በመግለጽም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ በመረዳዳት በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል አቅሙ የሌላቸውን ወገኖች ሊደግፍ እንደሚገባም ከተማ አስተዳድሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችን በከፊል ዘጋ፡፡
Next articleበታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽ ተማጽኖ እና የጀርመን አጸፋ!