
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ ለሁለንተናዊ እድገቷ እና የለውጥ ጎዳናዋ መፋጠን ጉልህ ድርሻ ያላቸው ውብ እና ማራኪ ገጽታን የተጎናፀፉ፤ እንዲሁም ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች የጥራት እና ፍጥነት ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ ነው፡፡
አሁን ላይ የዲፖ ቁጥር ሁለት እና ሌሎች በዚህ ዓመት የተጀመሩትን ሳይጨምር በከተማዋ ያለው አጠቃላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ሽፋን 683 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መኾኑ ተገልጿል፡፡ በሽፋን ደረጃም 99 በመቶ መድረሱ ነው የተነገረው።
👉145 ነጥብ 68 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣
👉185 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮብል ጌጠኛ መንገድ፣
👉15 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የጠጠር ጥርጊያ መንገድ፣
👉179 ነጥብ 91 ኪሎ ሜትር የሪዳሽ መንገድ ተገንብቷል፡፡
ከዚህ ባለፈ እንደ ከተማ አሥተዳደር 157 ነጥብ 01 ኪሎ ሜትር የመሬት ሥራ እንዲሁም 255 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ተፋሰስ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ በራስ የፋይናንስ ምንጭ እና የሰው ኀይል አቅም ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ ይገኛል ነው የተባለው።
የባሕርዳር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የከተማ አሥተዳደሩን የመንገድ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት ጠቅሶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው እንደ ከተማ አሥተዳደር ባለፋት ዓመታት አጠቃላይ ለመንገድ መሠረተ ልማት 11 ቢሊዮን 659 ሚሊዮን 601ሺህ 545 ብር ጥቅም ላይ መዋሉን ነው የገለጸው፡፡ ለዚህም ውጤታማነት የማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!