“የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በማንገብ አፍሪካን ለማስተሳሰር እየሠራ ነው” አቶ መስፍን ጣሰው

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካዊያንን እርስ በእርስ የማቀራረብ እና ከተቀረው የዓለም ክፍል ጋር የማስተሳሰር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ወደ ምዕራባዊቷ የአፍሪካ ሀገር ሴራሊዮን ፍሪታውን ከተማ አዲስ በረራ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ ነው ብለዋል።

በተለይም ደግሞ አየር መንገዱ የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ በማንገብ የአፍሪካ ሀገራትን እርስ በእርስ ለማስተሳሰር እየተጋ መሆኑን ነው የገለጹት። በዛሬው እለት ወደ ሴራሊዮን ፍሪታውን ከተማ የተጀመረው በረራ የዚሁ ማሳያ እንደኾነ ገልጸዋል። ዛሬ ወደ ሴራሊዮን የተጀመረው በረራ በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚደረግ ሲኾን የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በሳምንት ወደ ሰባት ጊዜ እንደሚያድግም ገልጸዋል።

በረራው የሴራሊዮን ዜጎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከአፍሪካ ውጭ ወደ እስያ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚያደርጉትንም ጉዞ የሚያሳልጥ ነው ብለዋል። በቀጣይም አየር መንገዱ አፍሪካን ከአፍሪካዊያን እና ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የጠቆሙት።

በኢትዮጵያ የሴራሊዮን አምባሳደር ሃሮልድ ቡንዱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሴራሊዮን ፍሪታውን በረራ መጀመሩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል። በተለይም ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲኹም በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማሳደግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በዛሬው እለትም አየር መንገዱ በረራ የጀመረባት የሴራሊዮን ፍሪታውን ከተማ በአፍሪካ 64ተኛ መዳረሻው መኾኗ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 በላይ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ገለጹ፡፡
Next articleበባሕርዳር ከተማ ለመሠረተልማት ሥራዎች ውጤታማነት የማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡