በቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር ) የተመራ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ልዑካን ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ አሥተዳደር የመሠረተ ልማት እና የልማት ትሩፋት ሥራዎችን ተመልክቷል ። ልዑካን ቡድኑ በ41 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኝ ድልድይ፣ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ የክልል በጀት እየተሠራ የሚገኝ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ኘሮጀክት እና የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ እና አልብኮ ወረዳን እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋጨፋ ወረዳን የሚያገናኘው እና በ41 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘውን የድልድይ ግንባታን የተመለከቱት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) የድልድዩ ግንባታ ሂደት በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከድልድይ ግንባታ በተጨማሪ ከተማ አሥተዳደሩ በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት። የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የቃሉ ወረዳ እና የሀርቡ ከተማ ለሌማት ትሩፋት የተመቸ ሥነምህዳር ያለበት በመኾኑ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ የክልል በጀት እየተሠራ የሚገኝ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ኘሮጀክት የመስመር ዝርጋታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲኾን የውኃ ማጠራቀሚያ ሪዘርቫየር ግንባታም እየተጠናቀቀ ይገኛል። የሀርቡ ከተማ ከንቲባ ያሲን አመዴ የውኃ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የውኃ ሽፋኑን አሁን ካለበት 43 ከመቶ በእጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል። በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቆ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙም ከንቲባው ተናግረዋል። የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቅቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ የሥራ ኀላፊዎቹ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡- ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን ለማምጣት አስታራቂ፣ ታራቂ እና አንቂ መኾን ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል”መንግሥቱ ቤተ፣ የደብረብርሃን ከተማ ምክርቤት አፈጉባኤ።
Next article“የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በማንገብ አፍሪካን ለማስተሳሰር እየሠራ ነው” አቶ መስፍን ጣሰው