“ሰላምን ለማምጣት አስታራቂ፣ ታራቂ እና አንቂ መኾን ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል”መንግሥቱ ቤተ፣ የደብረብርሃን ከተማ ምክርቤት አፈጉባኤ።

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

የደብረብርሃን ምክር ቤት “ሀገራዊ ማንነት እና ሀገራዊ እሴቶች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ “በሚል መሪ መልዕክት ያዘጋጀው የሰላም የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ አሰተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ እሴቶችን ለችግሮች መፍቻ አድርጎ በመጠቀም ረገድ ውስንነት የሚስተዋል በመኾኑ ለተግባራዊነቱ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

“እኔ” ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት በእኛነት መንፈስ ችግሮችን የመፍታት ልምድን ማዳበር ተገቢ መኾኑን አንስተዋል። የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰሎሞን ጌታቸው እንደ ሀገር የሚወሰዱ እሴቶችን በማጓልበት ለችግሮች መፍትሄ መስጠት ላይ መሥራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት ሊኾን ይገባል ብለዋል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን መታገል ያስፈልጋል ነው ያሉት። የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ መንግሥቱ ቤተ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም ሲቻል እንደኾነ አስረድተዋል። ሰላምን ለማምጣት አስታራቂ፣ ታራቂ እና አንቂ መኾን ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ብለዋል።

ቅንነት የተሞላበት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን በመዘርጋት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት መሥራት ይጠይቃል ሲሉ ዋና አፈጉባኤው ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ከሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ለሚመለከታቸው ፈጻሚ አካላት የሚያደርስ መኾኑም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ገንዘብ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሮችን ከኋላቀር አስተራረስ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ግብርና ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
Next articleበቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ገለጹ፡፡