
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ ግብርና ሜካናይዜሽን እንቅስቃሴ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉን (ዶ.ር) ጨምሮ የግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በምግብ ራስን ለመቻል፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት ለማቅረብ እና የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እውን መኾን የሚችለው በሜካናይዜሽን የተመራ ግብርና ማስፋፋት ሲቻል መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ በኩል እንደ ክልል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ በዚህም ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከመኸር፣ ከመስኖ እና ከበልግ እርሻ ተገቢውን ምርት ለማግኘት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ከዓመት ዓመት አዳጊ ውጤት ተመዝግቧል፣ ይህ ግን በቂ አይደለም ከዚህ በላይ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ እየተገበረ ያለው የኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሮች ተደራጅተው በዘመናዊ መንገድ እንዲያመርቱ የሚያደርግ በመኾኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በኩታ ገጠም መደራጀቱ አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች ማሳቸውን በፍላጎት በማቀናጀት በጋራ ምርታማነትን ለማሳለጥ ያስችላል። ይህም አርሶ አደሮቹ ኩታገጠም የኾኑ ማሳዎቻቸውን አገናኝተው፣ ትራክተሮችም ኾነ ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በግዥም ኾነ በኪራይ በጋራ እንዲያመርቱ እድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም አርሶ አደሮች ከኋላቀር አስተራረስ ዘዴ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው እና የክልሉን የሜካናይዜሽን ጉዞ እንዲሁም የአማራ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሲኔየር ዳይሬክተር ተሾመ ዋለ (ዶ.ር) በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የኢንስቲትዩቱ ሚና በተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ መጨረሻ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በአማራ ክልል ግብርና ትራንሰፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ድጋፍ የተገዙ 19 ትራክተሮች ለዩኒየኖች፣ ለማኅበራት እና ለተደራጁ ወጣቶች ርክክብ መደረጉን ከአማራበክልል ግብርና ቢሮ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!