ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወሳኝ በመኾኑ መደገፍ አስፈላጊ መኾኑን ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የኢትዮጵያን እድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ በመኾኑ ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የወልቂጤ እና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጸዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲኾን አሁን ላይም በአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፉን እያካሄደ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲኾን ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ያሉት ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር.) ናቸው። ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወሳኝ በመኾኑ መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነም ነው ያስረዱት። ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ስኬት የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ.ር.) በበኩላቸው የሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲኾን ለማድረግ በተለይም ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል። በተለይም ለሀገር ሰላም፣ እድገት እና ብልጽግና መሥራት እንደሚገባ እና ለዚህም ሁሉም ተመካክሮ፣ ሃሳብ አዋጥቶ እና ተግባብቶ መሄድ እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ ሲያስገነዝብ መቆየቱንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ኮሚሽኑን የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ እንደኾነ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የሰላም እና የልማት ሥራዎችን በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል” ደሳለኝ ጣሰው
Next articleአርሶ አደሮችን ከኋላቀር አስተራረስ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ግብርና ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡