
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ያግዛል ያለውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እያደረገ ስላለው ቅድመ ዝግጅት ዛሬ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በመግለጫው እንዳመላከተውም የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ከዛሬ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 24/2012 ዓም በከፊል ዝግ ይሆናሉ፡፡
የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ታደለ ልይለት እንደገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ውሳኔውን ያስተላለፈው በፍጥነት እየተሰራጨ ያለውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ነው፡፡
በሌላ በኩል ከመጋቢት 10/2012 ዓ.ም ጀምሮ በነጥብ ሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት ምደባ ዙሪያ በአካል፣ በግለሰብም ሆነ በቡድን የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የማይቀበል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ አሳማኝ ቅሬታዎች ሲኖሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በሚሰሩባቸው ተቋማት በኩል ቀርቦ ተቀበይነትን ካገኘ ደረጃውን ጠብቆ ሊታይ እንደሚችልም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲያግዝም ደንበኞች አግልገሎት ፈልገው ሲመጡ በተናጥል እንዲሆን አቶ ታደለ አሳስበዋል፡፡ በስልክ መረጃ መጠየቅንም አማራጭ ማድረግ እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑ ኮሮናን ለመከላከል በክልሉ የተቋቋመው ግብረ ሃይል አካል በመሆን እየሠራ እንደሆነ በመግለጽም ሠራተኞችም ዓርአያ መሆን እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው