
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በዕቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘውን የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ ሂደትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ግንቦት 21/2016 ዓ.ም የተጀመረው እና ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ያለው ምክክር በዛሬው ዕለት ተወካዮች በኅብረተሰብ ክፍል አደራጅተው የተጠናቀረ አጀንዳ በማውጣት ወደ ቀጣይ ክፍል የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች እንደሚለዩ አስረድተዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ተወካዮች በመደማመጥ ጊዜ ሰጥተው የተወያዩበት መሆኑን ጠቅሰው አጠቃላይ የምክክር ምዕራፉ በዕቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የኅብረተሰብ ተወካዮች በንዑስ ቡድን ተከፋፍለው ባደረጉት ውይይት የታየው መከባበር፣ መደማመጥ፣ ትዕግስትና ጥያቄና ሀሳቦችን በሠለጠነ መንገድ ማንሳታቸው ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል። ይህም ለሰላምና ለምክክር ያላቸውን ዝግጁነት ያሳየ መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ብሌን የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!