በዳንግላ ከተማ እና አካባቢው ሕዝባዊ የሰላም ምክክር ተካሄደ።

13

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዳንግላ ከተማ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ዛሬ ሕዝባዊ የሰላም ምክክር ተደርጓል። መድረኩን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው እና የ304ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል አዲሱ ሙሐመድ መርተውታል፡፡

በመድረኩም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር መከላከያ መኮንኖች፣ የክልል እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል። በመድረኩ የዳንግላ ከተማ እና አከባቢው እንዲሁም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለበት የሰላም ሁኔታ ሪፖርት ቀርቦ ምክክር ተደርጓል፡፡

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የዳንግላ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ እና ልማታዊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የዳንግላ እና አካባቢው ማኅበረሰብም የሚታወቅበትን የሰላም እሴት በማጎልበት አካባቢውን እየረበሹ ያሉ ጽንፈኞችን መታገል እንደሚገባው አሳስበዋል። ብርጋዴር ጀኔራል አዲሱ ሙሐመድ ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾን እና ጽንፈኛውን ነጥሎ መታገል እንዳለበት ነው ያብራሩት፡፡ ይህ ካልኾነ ሠራዊቱ ሕግን እንደሚያስከብር አስረድተዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው በመድረኩ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ተሰጥቶ ሕዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ ወደ መደበኛ ልማት እንዲገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ማምረት ሊገባ ነው፡፡
Next articleበአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ምዕራፍ በዕቅዱ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ኮሚሽኑ ገለጸ።