
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀጣይ ሁለት ወራት ወደ ማምረት እንደሚገባ ተገለጸ። የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኘ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በሀገሪቱ በሲሚንቶ ምርት፣ አቅርቦት እና ግብይት ከፍተቶች ይታያሉ፡፡ ይህም የምርት እጥረት የሚፈጥረው ክፍተት በርካታ ተያያዥ ችግሮችንም የሚያስከትል ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ወደ ማምረት እንደሚገባ ገልጸው ይህም አሁን ያለውን የሀገሪቱን የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት እስከ 40 በመቶ የሚሸፍን እንደሚኾን ተናግረዋል። ፋብሪካው የመጀመሪያውን ምእራፍ ሲያጠናቅቅ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን እንዲሁም ሁለተኛው ምእራፍ ሲጠናቀቅ በዓመት 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የሚያመርት መኾኑንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በረንታ የሲሚንቶ ፕሮጀክት አሁን በአካባቢው ያሉ ችግሮች ተፈትተው ወደ ማምረት ሲገባ በቀን ሰባት ሺህ በላይ ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት አመልክተዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ማምረት ሲገባ ደግሞ 23 ሺህ 400 ቶን ሲሚንቶ በቀን እንደሚያመርት ይጠበቃል ብለዋል። እነዚህ ውጤቶች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አበረታች አፈጻጸም ካስመዘገበባቸው መስኮች መካከል ይገኙበታል።
የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትን ለማሻሻል በተለያዩ ጊዜያት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን የጸጥታ እና ተያያዥ ችግሮች በቅርበት በመፍታት የተለያዩ ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ነጥብ 42 ሚሊዮን ቶን ለማምረት መቻሉን ገልጸው ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ22 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም በገበያ ላይ ተከስቶ የነበረውን የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት በተወሰነ ደረጃ ለማረጋጋት መቻሉን አመልክተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ተኪ ማዕድናትን በተመለከተም የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በዋናነት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጪ የሚያስገቡትን የከሰል ድንጋይ የመተካት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለድንጋይ ከሰል ተጠቃሚ ሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአጠቃላይ ፍጆታቸው 64 በመቶ ለመሸፈን መቻሉንም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!