
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ለእናት ሀገር ክብር፣ በቃል ኪዳን ለተሰጠች ሠንደቅ ፍቅር፣ የእናት እና የአባት እትብት ለተቀበረባት ሀገር ዳር ድንበር ሲሉ እንደታጠቁ ኖረዋል፣ ጎራዴያቸውን እንደሳሉ፣ ጦራቸውን እንዳሾሉ፣ ጠመንጃቸውን እንደወለወሉ፣ ጋሻቸውን እንዳሳመሩ ዓመታትን ተሻግረዋል። ወሰን እንዳይጣስ፣ ታሪክ እንዳይደመሰስ፣ ሃይማኖት እንዳይረክስ፣ ወንዙ በጠላት እግር እንዳይደፈርስ ሲሉ በአያሌ ጦርነቶች ዘምተዋል፣ ከጠላት ጋር ተናንቀዋል፣ በጠላት ሰፈር ያለ ፍርሃት ተመላልሰዋል፣ ሲሻቸው በፈረሳቸው እየሰገሩ፣ ሲሻቸው በእግራቸው እየተወረወሩ በእናት ሀገር የመጣውን ጠላት አንገት አስደፍተዋል። ፎክሮ የመጣውን አንበርክከው ምህረት አስለምነዋል።
ሀገራቸውን ባዕድ እንዳይደፍራት፣ በክፉ ዓይኑ እንዳያያት፣ በቀጣፊ እጁ እንዳይነካት፣ ለምድሯ ባልተገባ እግሩ እንዳይረግጣት፣ ሠንደቋን ዝቅ እንዳያደርጋት፣ ባሕልና ታሪኳን እንዳያጠፋባት በጀግንነት ተዋግተው፣ በጀግንነት መክተው፣ በጀግንነት ድል መትተው፣ የሀገራቸውን ዳር ድንበር አስከብረው፣ ወገኖቻቸውን አኩርተው፣ ጠላቶቻቸውን አሳፍረው፣ በግርማ እና በሞገስ ኖረዋል።
ሀገር ተነካች በተባለችበት አቅጣጫ ሁሉ ፈረሳቸውን ጭነው፣ ጦራቸውን አስከትለው በጀግንነት ዘምተዋል። በጀግንነት መገስገስን፣ በእግረኛ እና በፈረሰኛ የጠላትን ምሽግ ማፈራረስን፣ በጦር ሰብቆ በጎራዴ የጠላትን አንገት መቀንጠስን እንጂ ፈርቶ መመለስን አያውቁትም። ልባቸውን ፍርሃት አያውቃትም። እሞታለሁ የሚል ስጋት አይነካካትም። ይልቅስ በጀግንነት እንደመላች፣ በድፍረት እንደተከበረች ኖረች እንጂ። የነጻነት ፊታውራሪ፣ እናት ሀገር አስከባሪ፣ ባለግርማ ናቸው ንጉሥ ሚካኤል፡፡
እርሳቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ በደም የጸና ነጻነት ለትውልድ አስረክበዋል፡፡ ከክብሩ ዝንፍ የማይል ኩራት እና ክብር ለልጅ ልጅ አውርሰዋል፡፡ ምስጋናው ታደሰ (ዶ.ር) ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ በተሰኘው የታሪክ መጽሐፋቸው የልጅ ኢያሱ እና የወይዘሮ ስኂን አባት፣ የእቴጌ መነን አያት፣ የአጼ ዮሐንስ የክርስትና ልጅ፣ የአጼ ምኒልክ አማች የቀድሞው ራስ ሚካኤል የኋላው ንጉሥ ሚካኤል በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ከነበሩት ታዋቂ የክፍለ ሀገር ገዢዎች ግንባር ቀደሙ ናቸው ይሏቸዋል።
በ1870 ዓ.ም ሚካኤል ተብለው የራስነት ማዕረግ ከተሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ ወሎ ክፍለ ሀገርን 35 ዓመታት በራስነት አሥተዳድረዋል። የታሪክ ጸሐፊው ጣልያናዊው ፈርናንዶ ማርቲኒን ጠቅሰው ሲጽፉ መልከ መልካምና አስተዋይ ናቸው ይሏቸዋል። በባሕሪያቸውም ለጋስ፣ አርቆ አሳቢ፣ አስተዋይ፣ ቻይና ታጋሽ እንደኾኑም ይናገሩላቸዋል።
ሚካኤል በተበታተነ መልኩ በትንንሽ ሥርወ መንግሥታት ይተዳደር የነበረውን የወሎ ክፍለ ሀገር በአንድ ማዕከላዊ አሥተዳደር ሥር በማድረግ ለክፍለ ሀገሩ ፖለቲካዊ ውህደት ታላቅ ሚና ተጫውተዋል። የአሥተዳደር ዘመናቸው ሠላማዊ፣ የተረጋጋ እና ሽፍትነት የጠፋበት ዘመን እንደነበር ይነገራል። አገዛዛቸው ፍትሐዊ እና በአርያነት የሚጠቀስ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። ዳግማዊ ምኒልክም “አገዛዝስ እንደነ ሚካኤል” ብለው የመሰከሩላቸው ታላቅ ሰው እንደኾኑ ታሪክ ይናገራል።
ምስጋናው ታደሰ (ዶ.ር) ሲጽፉ ሰውነታቸው ግዙፍ ኾኖ ግርማ ሞገሳቸው ከሩቅ የሚያስፈራው የወሎው ባላባት ከልጅነታቸው ጀምሮ ፍርሃት የማይደፍራቸው ጀግና እንደነበሩ በስፋት ይነገርላቸዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ አሻራውን ጥሎ ያለፈ ሠራዊት በመገንባት ይታወቃሉ። ጀግና ጦረኛን መፍጠር የሚችሉት ጀግናው ጦራቸውን በጀግንነት፣ በብልሃት እና በቆራጥነት በመምራት በአያሌ ጦርነቶች ተሳትፈዋል። በሰአቲ፣ በመተማ፣ በዓድዋ በተደረጉ ሀገርን የመታደግ፣ ሠንደቅን የማስከበር፣ ጠላትን ለመሰባበር በተለያዩ ጦርነቶች ላይ ከሌሎች ጀግኖች ጋር በመኾን ተዋግተዋል። በኩራት ሄደው፣ በድል ደምቀው በክብር ተመልሰዋል።
ኢትዮጵያን ለመውረር፣ ኢትዮጵያውያንን ለማስገበር አልመው የመጡት ጣልያናውያን ጀግኖችን የኢትዮጵያ መሳፍንትን እና መኳንንትን በገንዘብ ሊገዙ፣ በሃብት ሊያታልሉ ይሞክሩ እንደነበር ይነገራል። ጣልያናውያን ራስ ሚካኤል እንዲገቡላቸው ማታለያ ካቀረቡላቸው ጀግኖች መካከል አንደኛው ነበሩ።
እርሳቸው ግን ለቃል ኪዳናቸው የሚታመኑ፣ ጀግና እና ብልህ ናቸውና አይኾንም አሏቸው። እርሳቸው ለሀገር መቁሰልን እንጂ ሀገር ማቁሰልን፣ ለሀገር ስጋቸውን መቁረስን እንጆ ሀገር መቁረስን፣ ለሀገር መሞትን እንጂ ሀገር መግደልን የማያውቁ እውነተኛ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸውና በጣልያናውያን ተሳለቁባቸው ይባላል።
ጀግኖቹ በጀግንነት ዘምተው፣ በጀግንነት ተዋግተው አዋግተው ድል አመጡ። ሀገር ለመውረር የመጣውን የጣልያን ወራሪ እንዳልነበር አደረጉት፡፡ ራስ ሚካኤል ከዓድዋ አስቀድሞ በአምባላጌ እና በመቀሌ በተደረጉ ውጊያዎች በኋላም በዓድዋ በጀግንነት የተዋጉ ጀግና እንደነበሩ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ፣ ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኙ መጽሐፍቶቻቸው ጽፈዋል።
በዓድዋው ጦርነት በመካከለኛው ግንባር ከገባው ጦር መካከል የራስ ሚካኤል ጦር አንደኛው እንደነበር ይነገራል። በዚህም ጊዜ ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የጠላትን ጦር ድባቅ የመቱ ጀግና ናቸው። በመካከለኛው ግንባር የነበረውን የጠላትን ጦር ከሌሎች ጀግኖች ጋር በመኾን ድባቅ ከመቱ በኋላ በምኒልክ ትእዛዝ አማካኝነት እነ ራስ አሉላ ወደ ነበሩበት ግንባር ሄደው ጠላትን ድባቅ እንዲመቱ ታዘዙ፡፡ በድል የተቋደሱት ጀግና በጀግንነት ደቆሱት፡፡ ወታደሩ ከመጀመሪያው ግንባር ወደ ሁለተኛው ግንባር ሲያቀና በጀግንነት እየፎከረ እና እየሸለለ እንደነበር ይነገራል።
“ማን በነገረው ለጣልያን ደርሶ
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ” እያለ የጀግናውን ጦረኛ ስም እያነሳ በጀግንነት ተዋጋ። በጀግንነትም ድል አደረገ። በሀገር ፍቅር ወኔ የተቆጣው የራስ ሚካኤል እና የራስ አሉላ ጦር የጠላትን ጦር አሸንፎ ጄኔራሉን ገደለ። እንደ ታሪክ ጸሐፊው ምስጋናው ታደሰ (ዶ.ር) ራስ ሚካኤል በሦስት ተከታታይ ነገሥታት በአጼ ዮሐንስ፣ በአጼ ምኒልክ እና በልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ በርካታ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተው አልፈዋል።
ከትንቢተኛው ሼህ ሁሴን ጅብሪል ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ሚካኤል ከእርሳቸው ጋር ስለ ክብር፣ ወደ ፊት ሊሆን ስለሚችለው ይወያዩ እንደነበር ይነገራል። ታዋቂው አባት ሼህ ሁሴን ጅብሪል ለእርሳቸው ልዩ ፍቅር እና አክብሮት ነበራቸው ይባላል፡፡
አጼ ምኒልክ እድሜያቸው እንደገፋ ጤናም እንደጠናባቸው ባወቁ ጊዜ ለልጅ ልጃቸው ለልጅ ኢያሱ ዙፋናቸውን አወረሱ። ልጅ ኢያሱ የአያታቸውን ዙፋን አደራ ወራሽ ኾኑ። ምኒልክ ሕመማቸው ጸንቶ አረፉ። እርሳቸው ካረፉም በኋላ መሣፍንቱና መኳንንቱ ንጉሠ ነገሥት ተብለው በአያታቸው ዙፋን እንዲቀመጡ ጠየቋቸው። ልጅ ኢያሱም “አባቴን ንጉሥ ሳላሰኝ ፈረሴን ከቀይ ባሕር ውኃ ሳላጠጣ ዘውድ ጭኜ ንጉሠ ነገሥት አልባልም” አሉ ይባላል፡፡
ልጅ ኢያሱ አባታቸውን ንጉሥ ለማሰኘት ወሰኑ። ይህንም ማድረግ የፈለጉበት ምክንያት ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ነው ይባላል። በእናታቸው የንጉሠ ነገሥት ልጅ የኾኑት ኢያሱ አባታቸውን ንጉሥ በማሰኘት የሁለት ነገሥታት ልጅ ለመባል ስለፈለጉ ነው። የታሰበው ኾነ። ራስ ሚካኤል ይነግሡ ዘንድ ቀን ተቆረጠ። በጦሳና በአዝዋ ታጅባ በኩራት የምትኖረው መናገሻቸው ደሴ ለንግሥ እና በዓል ሽር ጉድ አለች። መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ወይዛዝርቱ፣ ጎበዛዝቱ፣ ሊቃውንቱ፣ የጦር አበጋዞች፣ ደጋጎቹ የሀገሬው ሰዎች በመናገሻቸው ከተማ ተሰባሰቡ።
በ1906 ዓ.ም፣ በወረኃ ግንቦት፣ በ23ኛ ቀን በጳጳሱ በአቡነ ጴጥሮስ እጅ ተቀብተው “ሚካኤል ንጉሥ ወሎ ወትግሬ” ተሰኝተው ዘውድ ጫኑ። “ራስ ሚካኤል ርዕሰ መሳፍንት” የሚለው ማሕተማቸው ተቀየረ። ማሕተማቸው “ዘ ሥልጣኑ ጽሑፍ ዲበ መትከፍቱ ሚካኤል ንግሠ ፅዮን ንግሠ ወሎ ወትግሬ” በሚል ተተካ። በንግሥናቸው ቀን ሆጤ ተጨንቃለች። በሰው ተመልታለች። በጀግኖች ተከባለች። በባለ ግርማ ንጉሥ ተውባለች። ስለ ምን ቢሉ ንጉሥ ሚካኤልን የመሠሉ ባለ ግርማ ንጉሥ ነግሠውባታልና። ለንግሥናው ድምቀት ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘውድና ሌሎች የነገሥታት አልባሳት፣ ቁጥሩ የበዛ ለበን ጠመንጃ ተልኮ ነበር ይባላል። ንጉሡ በነገሡበት ቀን ለአምስት ደጃዝማቾች የራስነት ማዕረግ ሰጥተዋል፡፡
በዘመናቸው ቤተ መንግሥት እና አብያተክርስቲያናትን ያሳነጹት ንጉሥ ሚካኤል በኢትዮጵያ ታሪክ በቤተክህነቱም፣ በቤተ መንግሥቱም ታላቅ አሻራ አላቸው። ፍርድ የሚፈረድበትን፣ ፍትሕ የሚሰጥበትን፣ በዙፋን የሚቀመጡበትን፣ ከመኳንንቱ እና ከመሳፍንቱ፣ ከጦር አበጋዞች፣ ከእልፍኝ አስከልካዮች፣ ከአሽከሮች ጋር የሚኖሩበትን ቤተ መንግሥት ባማረ ቦታ ላይ የተዋበ አድርገው ሠርተዋል።
በቤተ መንግሥታቸውም ፍትሕን ብሎ ለመጣ ፍትሕ ሰጥተዋል፣ ቸግሮት ለመጣ አጉርሰዋል፣ አልብሰዋል። ታናሽ ታላቅ፣ የተማረ ያልተማረ እያሉ የማይከፋፍሉት፣ ሰውን በሰውነቱ የሚያከብሩት ታላቁ ሠው መታበይ ሳይታይባቸው ሁሉንም እንዳጎረሱ እና እንዳለበሱ ኖረዋል። አይጠየፉምና አይጠየፍን አሰርተው ፍቅርን ሰጥተዋል፣ ደግነትን አድርገዋል።
ታቦታት የሚያድሩባቸው፣ መንፈስ ቅዱስ የሚጸልልባቸው፣ ንዋየ ቅድሳት በክብር የሚኖሩባቸው፣ ኪዳን የሚደረስባቸው፣ ቅዳሴ የሚቀደስባቸው፣ ሥጋ ወደሙ የሚፈተትባቸው፣ ነፍስ የምትድንባቸው፣ ለሀገር ሰላምና ፍቅር የሚጸለይባቸው አብያተክርስቲያናትን አስውበው አሳንጸዋል። ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ቅርስ አስቀምጠዋል።
ንጉሥ ሚካኤል ከድሆች ጋር አብሮ መብላትን የማይጸየፉ፣ ምጽዋት መስጠትን የሚያዘወተሩ እንደነበሩ ታሪካቸው ይናገራል። ጀግንነት እና ሕዝብ ከማሥተዳደር ብልሃት በተጨማሪ ጠንካራ የጸሎት ሕይወት የነበራቸው ንጉሥ ሚካኤል በስዕል ቤት ማርያም በኋላም በቤተመንግሥታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ ባስገነቡት የጸሎት ቤታቸው በየዕለቱ ጸሎት ማድረግን ያዘወትሩ ነበር። በዕለተ ሰንበት ደግሞ በግሩም ሁኔታ ባሳነጹት የደሴ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ያስቀድሳሉ። ማዕዳቸውንም በካህን ሳያስባርኩ አይቆርሱም ነበር ይባልላቸዋል። እነኾ ንጉሥ ተብለው ዘውድ በጫኑባት በግንቦት 23 ታሪካቸው እየታወሰ፣ ለሀገር ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየተነሳ ይከበራሉ፣ ይዘከራሉ፡፡ ለሀገር ክብር አያሌ ታሪኮችን ሰርተዋልና ክብር ይገባቸዋል፤ ትውልድ ይኮራባቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!