
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ 11 የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከ2ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ከወከሉት የኀብረተሰብ ከፍል ይዘው በመጡት አጀንዳ ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል፡፡ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮቹ በዚህ ውይይታቸው እጅግ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ተወያይተዋል፡፡
በዛሬ የጠዋት መርሐ-ግብር አጀንዳዎቻቸውን በአንድ ቃለ ጉባኤ የሚያደራጁበት ኹነትም በግዮን ሆቴል እየተከናወነ ይገኛል። በተጨማሪም በሂደቱ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚያደርጓቸው የምክክር መድረኮች እያንዳንዳቸው 11 ተወካዮችን መምረጥ ጀምረዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በከተማ አሥተዳደር ደረጃ የሚካሄደው ምክክር ከየኅብረተሰብ ክፍሉ ወኪሎች በተጨማሪ የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እና ማኅበራት ተወካዮችን፣ የሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮችን እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማካተት ነገ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!