
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ “ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጲያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የጽዳት እና አረንጓዴ ልማት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረት ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ እንዲኹም ሌሎች የክልል እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
17 ማኀበራትን በማደራጀት በከተማዋ በሚገኙ ቀበሌዎች የጽዳት ሥራን እያከናወኑ መኾኑን የገለጹት የኮምቦልቻ ከተማ አካባቢ ጥበቃ የአረንጓዴ ልማት ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደሳለኝ እጅጉ ከተማዋን ጽዱ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህር እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቦታኒካል ጋርደን አመራር ኑሪያ አብዱረህማን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጋር በቅንጅት በመሥራት አካባቢውን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአካባቢውን ጸጋዎች በመጠቀም ለአካባቢው ነዋሪዎችም ኾነ ለጎብኝዎች ማራኪ የኾነ ቦታን ለመፍጠር ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ላይ እነደኾኑም ዶክተር ኑሪያ ለአሚኮ ተናግረዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ ኮምቦልቻ ከተማ የተፈጥሮ ጸጋን የታደለች በመኾኗ ይኽንን የገቢ ምንጭ ማድረግ የሁሉም ድርሻ ነው ብለዋል። አልሚ ባለሀብቶች በተለይም የአካባቢ ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ከተማ አሥተዳደሩ ቁርጠኛ መኾኑን ጠቁመዋል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረት ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጽዱ ከተማን ለመፍጠር አመራሩ ከማኀበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት ይገባዋል ብለዋል። “የአረንጓዴ ልማት ስፍራዎችን ለማስፋፋት ማነቆ የኾኑ አሠራሮችን መፍታት ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል። ዘርፉን ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሠራበት እንደኾነም በውይይት መድረኩ ላይ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!