
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባሕርዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን እያመረቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጥረት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በባሕርዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎቹ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማምረት በአነስተኛ ዋጋ እና በነፃ ለማኅበረሰቡ ለማከፋፈል ሥራ መጀመሩን የየኩባንያዎቹ ሥራ አስኪያጆች ገልፀዋል፡፡
የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይታየው አጥናፉ እስካሁን ከ2ሺህ በላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መመረቱን ገልፀዋል፡፡
የመግዛት አቅም ለሌላቸው የባሕርዳርና አካባቢዋ ነዋሪዎች በነጻ እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ከፋብሪካው ማኅበራዊ ኃላፊነቶች አንዱ እንደሆነ ነው ተወካይ ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
የበሽታውን የመስፋፋት ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ምርቱን በቀን በሦስትና በአራት እጥፍ ለማሳደግ እንደታሰበም አስታውቀዋል፡፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጨርቁ ዋጋ በፋርማሲዎች ከሚሸጠው እጅግ ያነሰ እንደሆነም አቶ ይታየው ተናግረዋል፡፡
የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በበኩሉ ከ100 ሺህ በላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማምረት ለማኅበረሰቡ በነፃና በአነስተኛ ዋጋ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጦፋ ጀማል ፋብሪካው ምርቶቹን የሚያዘጋጀው ከክልሉ ጤና ቢሮ ባገኙት የጥራት ደረጃ ምክረ ሀሳብ መሠረት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡