
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የዓለም ጤና ድርጅት አባል ሀገራት የዛሬን ቀን የዓለም ከትምባሆ ነጻ ቀን በሚል እንዲከበር የወሰኑት እ.አ.አ በ1987 ነበር። ዓላማቸውም በትምባሆ ምክንያት የሚመጣውን ሞት ለዓለም በማስገንዘብ ትምባሆን የመከላከል ሥራውን ማጠናከር ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን ቀን በተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች የሚያከብረው ሲኾን በተለይም ትምባሆን መጠቀም የሚያስከትለውን ጉዳት፣ የትምባሆን አምራች ድርጅቶችን የንግድ እንቅስቃሴ፣ የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ወረርሽኝን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት እንዲሁም የዓለም ሕዝብ ጤናው የተጠበቀ ሕይወት የማግኘት መብታቸውን እንዴት ማስከበር እንደሚችሉ እና የወደፊቱን ትውልድ ጤና እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ የሚያስገነዝቡ ትምህርቶችን ይሰጣል።
እኛም ቀኑን በማስመልከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካስቀመጣቸው እውነታዎች መካከል ጥቂቶችን እናጋራችሁ።
1. ትምባሆ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ሲኾን ከእነዚህ መካከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚኾኑት ትምባሆ የማያጨሱ ነገር ግን በሚያጨሱ ሰዎች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ናቸው።
2. በ2020 በተደረገ ጥናት በዓለም ላይ ከ22 በመቶ በላይ የሚኾን ሕዝብ የትምባሆ ተጠቃሚ መኾኑ ተረጋግጧል።
3. 80 በመቶ የሚኾነው ትምባሆ ተጠቃሚ የሚገኘው በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው።
4. እ.አ.አ በ2003 የትምባሆ ወረርሽኝን ለመግታት የዓለም የጤና ድርጅት አባል ሀገራት” የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ሥምምነት ማዕቀፍን” ተግባራዊ ለማድረግ ወስነዋል። በአሁኑ ወቅትም 182 የዓለም ሀገራት የዚህ ስምምነት አካል ስለመኾናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያስረዳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዛሬን ቀን “ከትምባሆ ነጻ ቀን” በሚል እያሰበው ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!