የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ32ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።

82

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ከነዚህም መካከል:-

1ኛ. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2ኛ. በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በኾነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማሥተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመኾኑ፤ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አሥተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የኾነ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3ኛ. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የደህንነት ስጋት ከመኾኑ በተጨማሪ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይኾን የሚያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4ኛ. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቀረበው አዋጅ ላይ ነው፡፡ የነዳጅ ውጤቶች ካላቸዉ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ አንጻር አቅርቦታቸውን፣ ክምችታቸውን፣ ስርጭታቸውን፣ ዋጋቸውን፣ ጥራታቸዉን እና ደህንነታቸውን መቆጣጠር አስፈላጊ በመኾኑ፤ እንዲሁም ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ ያለው ግብይት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ የኾነ የአቅርቦት ሰንሰለት እና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰው ተኮር የማኅበራዊ ድጋፍ ዘርፍ የአነስተኛ ወጪ ለአቅመ ደካሞች የሚዉሉ ቤቶች አሠራር ተግባራዊነት ለውጦች ተገኝተዋል።
Next article“ከትምባሆ ነጻ ቀን”