
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ተኮር የማኅበራዊ ድጋፍ ዘርፍ የአነስተኛ ወጪ ለአቅመ ደካሞች የሚዉሉ ቤቶች አሠራርን ከመሰረቱ እንዲለወጥ አድርገዋል። ይህ ጉልህ የአሠራር ርምጃ ከቤቶች ማደስ ባሻገር በእጅጉ የተጎሳቆሉ፣ በማይጠገኑበት ደረጃ ያረጁ፣ ለሰው ልጅ መኖሪያ ቀርቶ ለመቆያም አስጊ የሆኑ ደሳሳ ቤቶችን ለሰው ልጅ ክብር፣ ጤና እና ደኅንነት በሚመቹ ወጪ ቆጣቢ ቤቶች መተካቱ ነው። እነኝህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን የሚጠቅሙ ስሥራዎች መንግሥታዊም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በከተሞች እና ክልሎች ለተመሳሳይ ተግባር እንዲነሳሱ እና የብዙዎችን የኑሮ ደረጃ እና የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እንዲችሉ አነሳስተዋቸዋል።
”ለውጥ ከቅርቡ የሥራ እና መኖሪያ አካባቢ ይጀምራል” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እምነት በአዋሬ አካባቢ ፈጣን ለውጥ በተግባር ታይቷል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ የዚህ ዓመቱ የክረምት ቤት እድሳት ሥራ በይፋ ከሳምንት በፊት የተጀመረ ቢሆንም ከጥቂት ወራት በፊት በአካባቢው የተጀመሩት የእድሳት እና የሌሎች ሕንፃዎች ግንባታም በመፋጠን ላይ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!