”ሊገጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሥትና ኮሚሽን

15

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው ክረምት ሊደርስ የሚችልን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሥትና ኮሚሽን አስታውቋል። አቶ አድኖ ገብሬ በደራ ወረዳ የምጽሌ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ የጉማራ ወንዝ በሚፈጥረው ጎርፍ ጉዳት ከሚደርስባቸው መካከል ናቸው። በጎርፍ መጥለቅለቅ ጊዜ ሰብል እንደሚወድም እና የመጠጥ ውኃ ችግርም እንደሚያጋጥም ለአሚኮ ገልጸዋል።

በመጭው ክረምት ጉማራ ወንዝ ሞልቶ እንዳይፈስስ ግድብ እየተሠራለት መኾኑን የነገሩን አቶ አድኖ ኅብረተሰቡም ግድቡን እንደሚንከባከብ ገልጸዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የአደጋ መከላከልና ፈጣን ምላሽ ባለሙያ ተስፋዬ መስፍን በዞኑ 23 የጎርፍ ተጋላጭ ቀበሌዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በተካሄደ ጥናትም በርብ እና ጉማራ ወንዞች ሞልቶ መፍሰስ ምክንያት 93 ሺህ 368 ሕዝብ፣ 7 ሺህ 808 ሄክታር ሰብል እና 12 ሺህ 777 የመኖሪያ ቤት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሊኾኑ እንደሚችሉ መለየታቸውን የጠቀሱት ባለሙያው ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል በ25 ኪሎ ሜትር የወንዙ ዳር ግድብ እየተሠራ እና እየተጠገነ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቁ ከአቅም በላይ ከኾነ ለሚፈናቀሉ ሰዎች የመጠለያ፣ ምግብ እና ውኃ፣ የመድኃኒት እና የመጓጓዣ ዕቅድ ችግሩን ለመከላከል በተቋቋመው ግብረ ኀይል መታቀዱን ነው አቶ ተስፋዬ ያሳወቁት። በክልሉ በዘንድሮው ክረምት በ32 አካባቢዎች 460 ሺህ ሰዎች፣ 280 ሺህ እንስሳት እና 15 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳለባቸው በአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሥትና ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ ገልጸዋል።

ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከኾኑት ውስጥም 15 ሺህ ሰዎች ለሚኖሩበት አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በወቅቱ ለማጠናቀቅም እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። እንደ ድርቅ ሁሉ ለጎርፍ አደጋም ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከክልሉ ወረዳዎች ውስጥ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው ተጠንተው መለየታቸውንም ጠቅሰዋል። ለችግሩ ደረጃ በማውጣት ቀድሞ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

ከመንግሥት እና ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ 94 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በጀት ለ20 ተጋላጭ አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ሥራዎች በጀት መለቀቁን ተናግረዋል። አብዛኞቹ ወረዳዎችም በተለቀቀላቸው በጀት ሥራ እየሠሩ ሲኾን ያልጀመሩ መኖራቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቅሰዋል። በብዛት የጎርፍ ተጋላጭ ለኾኑ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ በጀት የተመደበ መኾኑን እና ማኅበረሰቡም በራሱ ሊሠራቸው የሚችላቸው ሥራዎች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ሊደርስ የሚችልን አደጋ ቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በየቀኑ በዝርዝር ክትትል እንደሚደረግባቸው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ሥራውን ያልጀመሩትን ግን በጀቱ ተነስቶ እጥረት ላለባቸው እንደሚመደብ አሳውቀዋል። ሁልጊዜ በጀት እየተመደበ በጎርፍ የተጎዱ ሰዎችን ከማቋቋም ይልቅ ጎርፍ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ምክንያቶችን ለይቶ መሥራት አዋጭ እንደኾ ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት አለመሥራት፣ የውኃ መፋሰሻዎችን አለመገንባት እና የተሠሩትም መዘጋት የጎርፍ አደጋ ምክንያቶች እንደኾኑ አስረድተዋል፡፡ እነዚህንም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብዙዎችን የሚቀጥፈው የጉበት በሽታ!
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰው ተኮር የማኅበራዊ ድጋፍ ዘርፍ የአነስተኛ ወጪ ለአቅመ ደካሞች የሚዉሉ ቤቶች አሠራር ተግባራዊነት ለውጦች ተገኝተዋል።