ብዙዎችን የሚቀጥፈው የጉበት በሽታ!

46

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጉበት በተላላፊ ቫይረስ እና ተላላፊ ባልኾነ አነሳሽ ምክንያት ሲጎዳ እና ሲቆስል የሚመጣ ህመም ነው የጉበት በሽታ ወይንም ሄፓታይተስ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመት የኅብረተስብ ክፍል በጉበት በሽታ (ሄፓታይተስ) ምክንያት ለሞት እንደሚዳረግ ከዚህ በፊት ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ሚኒስቴሩ እ.ኤ.አ የ2017 የተሠራውን የዳሰሳ ጥናት መሠረት አድርጎ ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ በሽታው በስፋት ተሰራጭቶ ከሚገኝባቸው ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡ በዓለም ላይ ተሰራጭተው በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙት ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ በመባል የሚታወቁት የቫይረስ አይነቶች መኾናቸውን ነው ሚኒስቴሩ የጠቀሰው።

የውስጥ ደዌ ፣ የጨጓራ፣ የአንጀት እና የጉበት ሳብስፔሻሊስት እና በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ክብረቴ ወልዴ (ዶ.ር) የጉበት በሽታ በሄፓታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ ቫይረሶች የሚመጣ በሽታ ነው። በተለይም ደግሞ ሄፓታይተስ “ቢ” እና “ሲ” ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገሮች ሥርጭቱ ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያም ከአጠቃላይ ሕዝቡ 10 በመቶ የሚኾነው የሄፓታይተስ ቢ በሽታ እንደሚኖርበት አንስተዋል።

ሄፓታይተስ ቢ ና ሲ ብዙውን ጊዜ በብዛት የሚከሰቱ እና ለተራዘመ ጊዜ ከሰውነት ጋር በመቆየት ወደ ውስብስብ የጤና እክል በመቀየር ጉበትን በሂደት የሚጎዱ ሲኾን ሌሎቹ ቶሎ ሊድኑ የሚችሉ ናቸው። ሄፓታይተስ በተለይም ደግሞ ቢ እና ሲ ቫይረሶች በተበከለ ደም ንክኪ፣ ንጽህናቸውን ባልጠበቁ ስለታማ መሳሪያዎች፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጊዜ፣ ልቅ በኾነ ግብረ ስጋ ግንኙነት፣ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ፣ በንቅሳት፣ በአካባቢ ንጽህና መጓደል ማለትም በተበከለ ምግብ እና ውኃ ሊመጣ ይችላል።

ምልክቶቹ ደግሞ እንደ በሽታው ደረጃ እንደሚለያይ አንስተዋል። የድካም ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ሙቀት ዋና ምልክቶቹ ሲኾን በሽታው እየጠነከረ ሲሄድ ደግሞ የሽንት መቀየር፣ አይን ቢጫ መኾን፣ የክብደት መቀነስ፣ ከፍተኛ የኾነ የድካም ስሜት ይከሰታል። ወደ ከፍተኛ ደረጃ እያደገ ሲሄድ ደግሞ ጉበትን በመጉዳት የሆድ መነፉት፣ የእግር ማበጥ፣ ደም ማስታወክ እና እራስን እስከ መሳት ሊያደርስ ይችላል።

በሽታው በሄፓታይተስ ቫይረስ የሚወጣ ኾኖ እያለ በማኅበረሰቡ ዘንድ በተለምዶ የወፍ በሽታ በሚል የሚሰጠው ስያሜ ስህተት ነው በለዋል ባለሙያው። በሽታው ከወፍ ጋር የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩ ብቸኛው የሕክምና አማራጩ ዘመናዊ ሕክምና መኾኑን አንስተዋል። እንደማንኛውም በሽታ በመንግሥት ወይንም በግል የሕክምና ተቋማት በዘመናዊ መንገድ ምርመራ እና ሕክምና እየተሰጠ ይሰጣል። ፈጥኖ ወደ ሕክምና መሄድ ከተቻለ መዳን የሚችል በሽታ መኾኑን ገልጸዋል። ባሕላዊ ሕክምና ለጉበት በሽታ እንደማይሠራ ያነሱት ዶክተር ክብረቴ ይባስ ብሎ ያልተመጠነ ባሕላዊ መድኃኒት በመውሰድ በሽታውን እያባባሰው እንደሚገኝ ነው የገለጹት። በሽታው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ እስከ 30 ዓመት ድረስ እንደሚቆይ የገለጹት ዶክተሩ በየጊዜው አጠቃላይ የጤና ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።

የጉበት በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቅድመ መከላከል እና ቀድሞ ችግሩን በመለየት ሕክምናውን በወቅቱ ማግኘት ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል። ከላይ መተላለፊያ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ነገሮች ራስን ማቀብ እንደሚገባም መክረዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሃኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን አለመውሰድ፣ ከአልኮል መጠጥ እና ከሱስ መራቅ፣ የግል እና የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅ፣ የመጠጥ ውኃን ንጽህና መጠበቅ፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግል እቃዎችን በጋራ አለመጠቀም፣ በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም እና ከሰውነት ፈሳሾች ንክኪ መቆጠብ እንደሚገባም መክረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን እና ባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ የግብርና ግብዓት በአርሶ አደሮች እጅ መድረሱ ተገለጸ።
Next article”ሊገጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሥትና ኮሚሽን