
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ የኢንስፔክሽን ቡድን በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን እና በባሕዳር ዙሪያ ወረዳ የግብርና ግብዓት አርሶ አደሮች እጅ መድረሱን ገልጿል፡፡
ቡድኑ በስፍራው ተገኝቶ የግብርና ግብዓት አቅርቦት የአፈጻጸም ሪፖርትን ነው የገመገመው። በውይይቱ ወቅት የዞኑ እና የወረዳው ግብርና እና ኅብረት ሥራ ኀላፊዎች በበጀት ዓመቱ የግብርና ሚኒስቴር እና ክልሉ ለማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ልዩ ትኩረት በመስጠት በፍጥነትና በብዛት በአርሶ አደሮች እጅ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
መሪዎቹ ስርጭቱ ከባለፉት ዓመታት በእጅጉ የተሻለ መሆኑን አንስተው የበቆሎ ምርጥ ዘር በተለይም የፓይነር ዝርያ በአርሶ አደሮች ፍላጎት ልክ አልቀረበልንም ብለዋል። ባለፈው ዓመት ከአፈር ማዳበሪያ እጥረቱ በተጨማሪ ፈተና የኾነ ሕገ ወጥ የማዳበሪያ ዝውውር እንደነበር አንስተዋል። በዚህ ዓመት ግን ሙሉ በሙሉ ችግሩ የተቀረፈ መሆኑን ተረድተናል ብሏል ቡድኑ። የመርከብ ዩኒየንን ማዕከላዊ መጋዘን በመጎብኘትም ሥርጭቱ ያለበትን ሁኔታ በአካል ተመልክቷል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የቡድኑ መሪ ጀምበር አያልነህ መንግሥትም ኾነ ግብርና ሚኒስቴር ከባለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተለየ ሞዳሊቲን በመከተል ከፍተኛ መጠን ያለዉ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ተገዝቷል ብለዋል። ከወደብ ወደ ክልሎችም መድረሱን እና የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት በዩኒየኖች እና በመሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አመካኝነት ፈጥነው ወደ አርሶ አደሮች እጅ ማድረስ መቻላቸውን በጥንካሬ አንስተዋል።
የቡድኑ መሪ ምርታማነትን ለመጨመር የተጀመረው ንቅናቄ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። በፀጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን ማዳበሪያ ያልቀረበላቸውን ወረዳዎችና ቀበሌዎች አማራጮችን ተጠቅሞ ማድረስ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። የዘር ጊዜ ለሚያልፍባቸው እና በክረምት የመንገድ ችግር ላለባቸው ቦታዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ የአፈር ማዳበሪያ የማስገባት ሥራ ሊከናወን ይገባል ብለዋል። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ሕገ ወጥ የአፈር ማዳባሪያ ዝውውር እንደይከሰት በተጀመረው መንገድ ጥብቅ ክትትል መደረግ እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል አቶ ጀምበር፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!