
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 540 ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተቋቋሙ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 210 ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመንግሥት ሠራተኞች የተቋቋሙ መኾናቸውን ከአማራ ክልል ኅብርት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ፋና የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር የመንግሥት ሠራተኛው እያጋጠመው ያለውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ሲባል አምስት የክልል ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ያቋቋሙት ማኅበር ነው፡፡ ፋና የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር ምንዳለም በላይ ማኅበሩ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የግብርና ውጤቶችን እና የፋብሪካ ውጤቶችን በተከታታይነት ለአባላቱ እያቀረበ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ማኅበሩ ለትርፍ ያልተቋቋመ ማኅበር በመኾኑ ለሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ለማቅረብ አቅደው እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት። ትርፍ ለማግኘት አንሠራም ብንሠራም ተመልሶ ለአባላቱ የሚከፋፈል በመኾኑ ሥራው ያለ ትርፍ ነው የሚሠራ ነው ያሉት። የመንግሥት ሠራተኛው የጋራ ችግሩን በጋራ ለመፍታት ያቋቋመው ማኅበር በመኾኑ ማኅበሩ የሠራተኞችን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሠጥቶ ይሠራል ነው ያሉት። ነጋዴዎች ሸቀጥ ሊያቀርቡ ይችላሉ።
ነገር ግን በብድር የሚሰጡት ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዎች ብቻ ነው። በመንግሥት ሠራተኞች የተቋቋሙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ግን የአባሎቻቸውን ችግር በተመሳሳይ ይፈታሉ ነው ያሉት። በመንግሥት ሠራተኞች የተቋቋሙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው እናት መሥሪያ ቤታቸው በበጀት ዓመቱ የሚመለስ ብድር እንደሚሠጣቸውም ጠቁመዋል። ይሕም ችግሩን ለመፍታት ቀለል እንዳደረገላቸው ጠቁመዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶችን ከፋብሪካ የሚያቀርቡ ከኾነ ዋጋው ሥለሚቀንስ በዝቅተኛ ደመወዝ የሚኖረው የመንግሥት ሠራተኛ ችግሩ በብዙ ይቃለልለታል ነው ያሉት። በሰላም እጦቱ ምክንያት የግብርና ምርቶችን ከሚፈልጉት ቦታ ማምጣት ባይችሉም ከተማው ላይ ካሉ ነጋዴዎች ዋጋ በማወዳደር የተሻለ የጥራት ደረጃ ያላቸውን ምርቶች እያቀረቡ ስለመኾኑም ነው ያስረዱት።
አቶ ምንዳለም በፋና የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ውስጥ 327 አባላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል በተደረገ ጥረት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን እና አባላትን ተጠቃሚ እያደረጉ መኾናቸውን ነው ያነሱት። በተለይ በዓል ሲመጣ እና ወቅቶችን መሠረት አድርገው ሸቀጦችን እንደሚያመጡ ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት።
የፋና የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ነው የነገሩን። የብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ሸማቾች ኀላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማኅበር በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የተቋቋመ የሸማች ማኅበር ነው፡፡
የብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ሸማቾች ኀላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማኅበር ጸሐፊ አዲሱ ጋሻው ማኅበሩ ለሠራተኞቹ በርካታ የኾኑ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን እያቀረበ መኾኑን ተናግረዋል። ማኅበሩ ላለፉት ሦስት ዓመታት የራሱ ካፒታል ሥላልነበረው ሸቀጦችን ለማምጣት ከሠራተኞች ገንዘብ ተሠብሥቦ እንደኾነም ነው የጠቀሱት።
ማኅበሩ የአዋጭነት ጥናት አስጠንቶ፣ ዓመታዊ ዕቅድ አቅዶ እና መተዳደሪያ ደንብ አጸድቆ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም ነው የተናገሩት። በቀጣይ ማኅበሩ ሁለት ሱቆችን በመክፈት፣ መጋዝን እና ቋሚ ሠራተኛ በመቅጠር አባላቱ የተለያዩ ሸቀጦችን ከማኅበራቸው እንዲያገኙ ለማድረግ መታቀዱን ነው የተናገሩት
ወይዘሮ ህሊና አገኘው በፋና የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ናቸው፡፡ ማኅበሩ የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን እያመጣ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮዋ እንደነገሩን ማኅበሩ ባመቻቸው የፍጆታ እቃ ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነቱን መቀነስ እንደቻሉ ነግረውናል፡፡ ማኅበሩ በብድር እቃዎችን እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል፡፡ ባንድ ጊዜ መግዛት የማይችሉትን ነገር በብድር ማግኘታቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን በአሚኮ የብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ሸማቾች ኀላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ማኅበሩ ለአባላት ጤፍ በሁለት እና በሦስት ወር የሚከፈል ፊኖ ዱቄት፣ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ስኳር እና ዘይት የመሳሰሉ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦችን እያመጣ ያከፋፍላል ይላሉ፡፡ ማኅበሩ በራሱ በጀት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ገንዘቡ ከአባላቱ ኪስ ወጥቶ ምርቱ እንደሚመጣም ነው የተናገሩት፡፡
ማኅበሩ ከኮብል ኢዱስትሪያል አክሲዎን ማኅበር እና ከባንኮች ጋር ውል በመውሰድ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና የቤት ቁሳቁስ ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ነግረውናል፡፡ በቀጣይ ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡ የፍጆታ ቁሳቁሶችንም በየወሩ እና በየሁለት ወሩ ቢያመጣ እና አባላቱን ተጠቃሚ ቢያደርግ ሲሉም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ በአማራ ክልል 540 ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መቋቋማቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 210 ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመንግሥት ሠራተኞች የተቋቋሙ መኾናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዋጋን በማረጋጋት በኩል ሰፊ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስረድተዋል። ገበያ የማረጋጋት ሥራው በርእሰ መሥተዳድሩ ሳይቀር ድጋፍ የተቸረው መኾኑንም አቶ ጌትነት አንስተዋል። በአንዳንድ ዞኖች ላይ ሸማች ማኅበራት ባይኖሩም ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ሥራ የሚሠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማሻሻያ እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። እነዚህን ማኅበራት በገንዘብ በመደገፍም የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ ማድረግ ተገቢ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በቀጣይ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር ያላቋቋሙ ቢሮዎችን እና መምሪያዎችን እንዲያቋቁሙ ግንዛቤ እየተፈጠረ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!