
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በፍላቂት ገረገራ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ የጸጥታ ችግር ከከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በሕዝባዊ የውይይት መድረኩ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመላ ኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች እንጂ ጦርነትን አማራጭ አድርገው ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ጥቂት የታጠቁ ኃይሎች አለመኾኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ኃይሎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉ ሁሉም የኅብረተሰብ አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። እንደተሳታፊዋቹ ገለጻ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ወደ ቀደመ ሰላማችን ለመመለስ የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በየደረጃው ማካለሉ ሕዝብ ጋር በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
እናቶች የጦርነትን አስከፊነት እንዲሁም የሚያስከትለውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በውል ተረድተው ወደ ጫካ የገቡ ልጆቻቸውን በመመለስ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል። ያለ ሰላም ምንም አይነት ነገር መሥራት እንደማይቻል የተናገሩት ተሳታፊዋቹ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸው ከፍተኛ ስለኾነ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ውለው ያደሩ የተለያዩ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላማዊ መንገድ በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ እንጂ በጦርነት አለመኾኑን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፋንታው (ዶ.ር) ተናግረዋል። ክልሉ ብዙ ችግሮች ተጋርጠውበት የነበሩ እና ከችግሮቹ ለመውጣት እየሠራ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ገጥሞናል፤ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመኾናቸው ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በሂደት እንጂ በጦርነት አማራጭ አለመኾኑን አሳስበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በክልላችን የተፈጠረው የሰላም እጦት ሕዝባችንን ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ዳርጎታል ብለዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍ፣ ጥያቄዎቹን ለመመለስ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከጦርነት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትና ምክክር አይነተኛ መፍትሔ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ተስፋሁን ተሰማ እንደተናገሩት የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ሽፋን በማድረግ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ጫካ በገቡ የታጠቁ ኃይሎች አላማ ተታለው አላማ የሌሌው ጦርነት በማካሄድ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እየተከፈለ በመሆኑ ወጣቶቻችን እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፍላቂት ገረገራ ከተማ ከንቲባ አንደበት ተስፋየ እየገጠመን ያለው የሰላም መደፍረስ ተረጋግተን ሕዝባችን የሚጠቅም የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባሮችን በአቀድነው ልክ እንዳንፈፅም እንቅፋት ኾኖብናል ነው ያሉት። በችግር ውሰጥም ኾነን የገጠመንን ቀውስ የመቀልበስና ወደተሻለ የልማት እንቅስቃሴ በመግባት በጊዜ የለኝም ስሜት ከሕዝባችን ጋር በመኾን ከተማችን ላይ የከፋ ችግር እንዳይፈጸም ማድረግ ችለናል ብለዋል።
ቀጣይም ከዚህ ቅን ሕዝባችን ጋር እንደከዚህ በፊቱ በመደጋገፍ የሚገጥሙንን ችግሮች በውይይት እንፈታለን ብለዋል። ጫካ ያሉትን ኀይሎች በመምከር የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ በማድረግ የአካባቢያችን ሰላም አስጠብቀን ለልማትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት አበክረን እንሠራለን ማለታቸውን ከመቄት ወረዳ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!