
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) እንዲሁም የፌዴራል፣ የክልል፣ የደብረ ብርሃን ከተማ እና የሰሜን ሸዋ ዞን የሥራ መሪዎች በተገኙበት የመነሻ ሪፖርት ቀርቦ የቀጣናውን የሰላም እና የልማት ሥራዎች ተገምግመዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ በድሉ ውብሸት የማኅበረሰባችንን ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ መሠረት ልማቶችን ለማጠናቀቅ በንቅናቄ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሰላምን ለማጽናት የሕዝብ ግንኙነት፣ የፈጻሚ መዋቅርን እግር መትከል ላይ በትኩረት የተሠራ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እንደከተማ በሰው ተኮር ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ የመሪዎች ቅንጅታዊ ሥራ በሰላም እና በልማት ውጤት ማምጣቱን አመላክተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የዞኑን እና የከተማውን የልማት እና የሰላም አፈጻጸም ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። እንደዞን የጸጥታ መዋቅርን እግር ለመትከል እና ቅንጅትን ለማሳደግ የበለጠ ይሠራልም ሲሉ አመላክተዋል። የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ “በቀጣናው ለሰላም እና ለልማት ሥራዎች ውጤታማነት የሥራ መሪዎች፣ የኅብረተሰቡ እና የጸጥታ መዋቅሩ ቅንጅት ሚናው ከፍተኛ ነው” ብለዋል። በቀጣናው ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላው ምዕራፍ ተደማሪ ለውጥ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
የሕዝብ ግንኙነት እና የመዋቅር አደረጃጀት እግር መትከልን እንዲሁም የልማት ሥራዎችን በተደማሪ ምዕራፍ የበለጠ መፈጸም እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። እንደ አማራ ክልል የጽንፈኛ ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሎጅስቲክ ክንፉ፣ የሚዲያ እና የፕሮፖጋንዳ አቅሙ እየተዳከመ መሆኑን አንስተዋል። በመጨረሻም የፌዴራል ሱፐርቪዥን ድጋፍ እና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል። መረጃው የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!