
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር ዘጠኝ ተቋማቶች በትራንስፖርት እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በቀረቡ ጥናቶች ላይ ውይይት አድረገዋል። በውይይቱም በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ለተቋም ግንባታ፣ ቅንጅታዊ አሠራር እና ቴክኖሎጂ ለተሻለ አፈጻፀም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። ኀላፊው የትራንስፖርት ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው፣ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አማራጮችን አስፍቶ በተመረጠ ሞዴል ከተማ ወደ ትግበራ ስለሚገባበት እና በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ማዘጋጀት እንደሚገባ ተስማምተናል ብለዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍም የሀብት አቅምን ለማወቅና ለመለየት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ላይ የተመላከቱትን ቀጠናዎች መነሻ በማድረግ በቀጣይ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተለይተው ባለሀብቱን ማበረታታት እና መደገፍ በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያይተን ወደ ትግበራ ለመግባት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል ሲሉ ገልጸዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ እንደ ቤት እድሳት፣ የአካባቢ ፅዳት፣ የመሳስሉ ተግባራት ላይ የክላስተራችን ተቋማት አመራሮች ከሠራተኞቻቸው ጋር በመሆን በቅርቡ ወደ ተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች በመሄድ ወደ ተግባር ስለሚገባበት መነሻ ዕቅድ ተወያይተን ለተግባራዊነቱ ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ኀላፊዉ በውይይቱ ለተሳተፉ የጥናት አቅራቢዎች፣ አመራሮች እና ሠራተኞች ላደረጉት የበሰለ ውይይት እና ተሳትፎ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ለትግበራው አብረን ልንተጋ ይገባል ሲሉ መልእክት ማስተላለፋቸውን ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!