“የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ሰላም አይተኬ ሚና አለው” አሕመዲን መሀመድ (ዶ.ር)

39

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩን (ዶ.ር)፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች በኮምቦልቻ ከተማ በምሽት እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ ለሰላም መጠበቅ ዓይነተኛ ሚናን በመጫወቱ አካባቢው ሰላም እንዲኾን እስከ ምሽት ድረስ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን ማስቻሉን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ገልጸዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ሰዎች በነፃነት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይሠሩ፣ ምርቶች እንዳይንቀሳቀሱ እንዲሁም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዳይጠናቀቁ አድርጓል ብለዋል፡፡

ዶክተር አሕመዲን ክልሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲመለስ እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ሰላም ወሳኝ እንደኾነ አስረድተዋል። በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ችግሮችን በግጭት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአካባቢው ሰላም መኾን የልማት ሥራዎችን በምሽት ሳይቀር ለማከናወን ማስቻሉን ጠቁመዋል።

መንግሥት ሁልጊዜም ቢኾን ጥያቄ አለን የሚሉ አካላትን ለመስማት ዝግጁ ነው ያሉት ዶክተር ዘሪሁን ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ምሁራን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮዽያ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።
Next article“በምሽት ፕሮጀክቶችን የመከወን ልምድ በውስን ከተሞች እየተሠራ ቢሆንም በሁሉም ከተሞቻችን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይኾንም” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)