
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በጫካ የነበሩ ታጣቂ ኀይሎች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል። የመንግሥት የሰላም ጥሪን ተቀብለው የተቀላቀሉ አካላትም ለሰላም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለተደረገላቸው የሰላም ጥሪ መንግሥትን አመስግነው በቀጣይ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው መደበኛ ሥራቸውን እንደሚጀምሩም ነው የገለጹት። ሌሎች አካላትም መንግሥት ያመቻቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስማረ የኋላሸት በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንደገቡ ገልጸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ተገቢ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለተቀላቀሉት አካላትም ከአቀባበል ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋና አሥተዳዳሪው አብራርተዋል። የ78ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ግርማ መሐመድ ለወረዳ ብሎም ለክልል ሰላም ዘብ መቆም፣ ለሰላም መዘመር ያለበት የሀገር የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ሳይኾን ሁሉም ሰላም ወዳድ የኅብረተሰብ ክፍል መኾን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያመላክተው ዋና አዛዡ ሰላም ሲሰፍን የመጀመሪያ ተጠቃሚው ሕዝብ ነውና ሠራዊታችን በየግዳጅ ቀጠና ሁሉ የማኅበረሰቡን ከሰቆቃ በመታደግ የሕዝብ አለኝታነቱን ያስመሰከረ ነው ብለዋል። የሕዝቡን ሰላም ለማምጣት እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በፅናት የሚታገል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!