
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ወረዳ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት በመከፈቱ የሰቆጣን እና የአካባቢውን ሕዝብ እያገለገለ ይገኛል። በአካባቢው ከተፈራ ኅይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ውጭ መንግሥታዊ የመድኃኒት ቤት ባለመኖሩ በመድኃኒት እጦት ሲቸገሩ መቆየታቸውን የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ወይዘሮ ደስታ ቢምረው የጤና መድኅን ተጠቃሚ ኾነን ከግል መድኃኒት ቤቶች ከፍተኛ ወጭ ስናወጣ ነበር ፤ አሁን ግን በጤና መድኅን ካርድ በነጻ አገልግሎት እንድናገኝ አድርጎናል ብለዋል። ለቀጣይም አገልግሎቱ ሰፍቶ እንዲቀጥል ከሆስፒታሉ የሌሉ መድኃኒቶች እንዲገዙ ጠይቀዋል። ሌላኛው ሀሳብ ሰጭ አቶ በላይ ንጉስ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት መከፈቱ ማኅበረሰቡ ጤንነታቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በሌሎች ወረዳዎችም ከጤና መድኅን ጋር በመቀናጀት መሰል ተቋማትን ቢከፍቱ መልካም ነው ብለዋል።
በአካባቢው ያለውን የመድኃኒት ቤት እጦት ለመሸፈን የተመሠረተ መኾኑን የጠቀሱት ደግሞ በሰቆጣ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት ተወካይ ዘውዱ ሙላው ናቸው። በቀንም ከ5 እስከ 100 የሚደርሱ ተገልጋዮች ይስተናገዳሉ ብለዋል። የሰቆጣ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስምረው ገዳሙ መድኃኒት ቤቱ ለሰቆጣ እና አካባቢዋ ማኅበረሰብ የተቋቋመ ቢኾንም በዋግ ኽምራ ለሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እያገለገለ እንደኾነ አስገንዝበዋል። በቀጣይም ተቋሙን በማሰፋት የኅብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ተገልጋዮች የጤና መድኅን አገልግሎት ለማግኘት መጥተው ያልተፈለገ ወጭ ማውጣት የለባቸውም ያሉት ኀላፊው የዋግ ኽምራን ሕዝብ ለማገልገል በርትተው እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!