የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ።

66

አዲስ አበባ: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች አስረክቧል። የመኖሪያ ቤቶች ባለ ዘጠኝ ወለል ሁለት ሕንጻዎችን ያካተተ ነው። በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ይህ “በጎነት የመኖሪያ መንደር” 140 ቤቶችን ያካተተ ሲኾን ዛሬ ለ117 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች ተሰጥቷል። ቀሪዎቹ 23 ቤቶች ደግሞ በልማት ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች የሚሰጡ ናቸው።

በጎነት የመኖሪያ መንደር የሕጻናት ማቆያ፣ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት የሚውሉ እና ነዋሪዎች የሚጠቀሙባቸው መሥሪያ ቦታዎች ተሟልተውለታል። ቤቶችን ሠርቶ ለማስረከብ ስምንት ወራት መፍጀቱን የተናገሩት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጀማል አሕመድ ቤቶቹ ለመኖሪያ ብቻ ሳይኾኑ ለነዋሪዎች የመሥሪያ ቦታም ያላቸው ናቸው ብለዋል።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ከሁለቱ ሕንጻዎች በተጨማሪ ሌላ አንድ ተጨማሪ ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንጻ በበጎነት የመኖሪያ መንደር ውስጥ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የመኖሪያ ቤቶችን ቁልፍ ለነዋሪዎች ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ልማት በሌሎች ጉስቁልና ላይ መኾን የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።

የከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች የሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚፈጥር “ሰው ተኮር” እንዲኾን እየሠራን ነውም ብለዋል። በቀጣይም የአዲስ አበባ ከተማ ልማት በሚሠራበት ወቅት ኅብረተሰቡ መጡብኝ ሳይኾን መጡልኝ እንዲል ከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል። የመኖሪያ ቤት ግንባታ ጥያቄን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በአጭር ጊዜ ሠርቶ ያስረከበን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው ሲሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- አደራው ምንውዬለት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የኮምቦልቻ ሲቲ ሴንተር የገበያ ማዕከል ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡
Next articleየማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት መከፈቱ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ እንዳገዛቸው የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።