
ደሴ: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ እንዲሁም ሌሎችም የክልል አመራሮች ናቸው፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሏቸው ብለዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ አሥተዳደሩ ፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደረግ ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ የጌታቸው፣አሕመድ እና ጓደኞቻቸው የገበያ ማዕከል ግንባታ ኅብረት ሽርክና ማኅበር የተሰኘ ሲኾን በ314 የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የተቋቋመ ነው፡፡ ማኅበሩ በሚያስገነባው ቅይጥ አገልግሎት ሕንፃ የማኅበሩ አባላት የራሳቸው መሥሪያ ቦታ እና ቋሚ ሃብት እንዲኖራቸው ከማድረጉ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለጸው፡፡
ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ዘመናዊ የቢዝነስ ማዕከል ኾኖ ያገለግላልም ተብሏል፡፡ ሕንፃው የሚያርፍበት የቦታ ስፋት 12 ሺህ 803 ካሬ ሜትር ሲኾን የግንባታ ወጭውም 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ነው የተባለው፡፡ የገበያ ማዕከሉ ግዙፍ እና ዘመናዊ በመኾኑ ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አርዓያ የሚኾን እና ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ ከመኾኑ የተነሳ ዓለም አቀፍ ንግድን የሚያሳልጥ እና የሚስብ ነው ተብሏል፡፡
ይህ የገበያ ማዕከል ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 1ሺህ 214 ሱቆች፣ 2 ሲኒማ ቤቶች፣ 2 ዘመናዊ የመሠብሠቢያ አዳራሽ፣ 5 ካፍቴሪያ፣ 103 ካሬ ሜትር ባለ ሦስት መኝታ፣ 324 መኖሪያ ቤቶች፣ 150 ቢሮዎች፣ 150 መኪኖችን የሚያቆም ፓርኪንግ፣ ጅም፣ ሬስቶራንት፣ ሱፐር ማርኬት፣ 14 የሕዝብ የመፀዳጃ ቤቶች፣ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ በቂ ቦታ እንደሚኖረው እንዲሁም በጊዜያዊነት 265 እና በቋሚነት ለ100 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የማኅበሩ ምክትል ሠብሣቢ ተመስገን ቢኾነኝ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!