
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ዛሬ የ “ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ” ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየምን አስጀምረዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የምታደርጋቸው ጥረቶች እንደዚህ ያሉ ትልልቅ መድረኮችን በላቀ ሁኔታ ለማስተናገድ የምትችልበትን አቅም እየገነቡላት ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ መርሐ ግብር ከ24 ሀገራት የተውጣጡ 115 ዓለም አቀፋዊ እና 41 የሀገር ውስጥ ተቋማት ተሳትፈዋል። ባለፈው ዓመት ከነበረው በበለጠ በዚህ መድረክ ከ8ሺህ 300 በላይ ባለድርሻዎች መካፈላቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያመለክታል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አውደ ርዕዩ በትብብር የመሥራት አድማሳችንን ማስፋት ብቻ ሳይኾን በኮንስትራክሽን እና ልማት ያለንን ፀጋ አውጥተን እንድንጠቀም በእጅጉ ይረዳናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ የዛሬው የ’ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ’ መድረክ ከግንባታ ማዘመን እስከ አገልግሎት ያለውን ሂደት በማሳደግ ስማርት ሲቲን ለመገንባት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት የሚገኝበት ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!