
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ያደረገው አፍሉዌንስ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ቀዳሚ ሥራዎችን አጠናቅቆ በባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት ፈጽሞ በባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ቀዳሚ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው አፍሉዌንስ የተሰኘው ኩባንያ ምርት ማምረት መጀመሩ ተገልጿል።
ኩባንያው የተለያዩ ትራንስፎርመሮችን እና ዲጂታል ቆጣሪዎችን በማምረት ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያቀርብ መኾኑ ተገልጿል። ኩባንያው በ725 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ ተረክቦ ወደ ሥራ መግባቱን እና በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከ300 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥሩየ ቁሜ ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከኮርፖሬሽኑ ጋር የውል ስምምነት የተፈራረሙ ባለሃብቶችን በአጭር ጊዜ ወደ ምርት ሂደት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መኾኑም ተጠቅሷል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ባሕር ዳር፤ ኮምቦልቻ እና ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ለኢንቨስትመንቶቹ መሳካት እና ፍስሰት መጨመር ሰላም ትልቅ ድርሻ ያለው በመኾኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን በማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾን እንዳለበት መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!